በሊዮኔል ሜሲ እና ላሚን ያማል መካከል ያለው አስገራሚ የ“19 ቁጥር” ምስጢር

0
170

 

በእግር ኳሱ ዓለም የሊዮኔል ሜሲ እና የላሚን ያማል ትይዩ የሕይወት ጉዞ አዳዲስ ገጾችን እየገለጠ የዓለምን ስፖርት ቤተሰብ ቀልብ መግዛቱን ቀጥሏል። በእነዚህ ሁለት የላማሲያ ፍሬዎች መካከል ያለው ትስስር ከተራ አጋጣሚ በላይ ኾኖ በ19 ቁጥር ላይ ያረፈ ይመስላል።

ይህ ቁጥር በሁለቱ ድንቅ ተጫዋቾች የእግር ኳስ ዘመን ውስጥ መልኩን እየቀያየረ በተደጋጋሚ ብቅ ማለቱ ቆም ብሎ በጥሞና ለሚያስተውለው ሰው ትልቅ እንቆቅልሽ ኾኗል።

የዚህ ሁሉ ትስስር መነሻ ወጣቱ ሜሲ ሕፃኑን ላሚንን በገንዳ ውስጥ በፍቅር ሲያጥብ የታየበት ያ ታሪካዊ ፎቶግራፍ ነበር። ከዚህ ድንቅ ትዕይንት ወዲህ እነሆ ዛሬ 19 ዓመታት ተቆጥረዋል። በወቅቱ የዓለምን ትኩረት ስቦ የነበረው ያ ምስል፤ ከ19 ዓመታት ረጅም ጉዞ በኋላ ዛሬ ላይ ያ ሕፃን አድጎ፣ ያም ወጣት ጎልምሶ፣ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ፍልሚያ ላይ ሀገሮቻቸውን ወክለው ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት እንዲገናኙ አድርጓቸዋል።

በሁለቱ ተጫዋቾች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርጉት ደግሞ ሁለቱም ተጫዋቾች በዓለም ዋንጫ ታላቁ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራቸውን ወክለው የተጫወቱት ገና በ19 ዓመት ዕድሜያቸው ነው።

በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታቸው ላይ ሁለቱም የለበሱት የ19 ቁጥር ማሊያን ነበር።

ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ሜሲም ኾነ ያማል የ19ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከበሩት በዓለም ዋንጫ ውድድር ወቅት መኾኑ ነው።

ሜሲ በባርሴሎና ቤት የ30 ቁጥር ማሊያ በመልበስ መጫወት ቢጀምርም፣ ብዙም ሳይቆይ ግን ወደ 19 ቁጥር ተሻግሮ ነበር። እነዚህ የግራ እግር ተጫዋቾች በካታሎኑ ክለብ ታዋቂውን የ10 ቁጥር ማሊያ ከመረከባቸው በፊት የለበሱት ይኸው የ19 ቁጥር ማሊያን ነበር። የባርሴሎናው ታዳጊ ያማል ይህንን ቁጥር ለመልበስ የወሰነው የሜሲን ቀደምት የእግር ኳስ አሻራ ለማክበር እንደኾነ ማርካ አስነብቧል።

ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ እና የመጨረሻ ማጠቃለያ የሚያደርገው ደግሞ፣ ሁለቱ ተጫዋቾች ሀገራቸውን ወክለው የሚሰለፉበት እና በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የሚገናኙበት የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የሚካሄድበት ቀን እ.ኤ.አ. ሐምሌ 19 መኾኑ ነው።

#AMECO #world #ስፖርት

#አዲስ_አበባ፡ሐምሌ11/2018 ዓ.ም

በሀብታሙ ዳኛቸው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here