ስዊዘርላንድ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ተጋጣሚዋቻቸውን አሸነፉ።

0
97
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ2026 የዓለም ዋንጫ ምድብ ሁለት ሁለተኛ ጨዋታ ስዊዘርላንድ ቦስኒያ ሄርዞጎቪናን 4 ለ 1 በኾነ ውጤት በመርታት ወደ ቀጣዩ ጥሎ ማለፍ ደረጃ ለመሸጋገር ትልቅ ዕድል ፈጥራለች።
በሎስ አንጀለስ በተደረገው በዚህ ጨዋታ እስከ 73ኛው ደቂቃ ድረስ ብዙም ሳቢ እንቅስቃሴ ያልታየበት ቢኾንም በ73ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የ20 ዓመቱ ወጣት ጆሃን ማንዛምቢ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን አቀጣጥሏል።
ከግቧ መቆጠር ማግስት የቦስኒያው ተከላካይ ታሪክ ሙሃሬሞቪች በስዊዘርላንዱ አጥቂ ላይ ጥፋት በመፈጸሙ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ይህም ስዊዘርላንድ ሌሎች ግቦችን እንድታስቆጥር ምክንያት ኾኗል። የቦስንያን ብቸኛ ግብ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨማሪ ደቂቃ ማሐሚክ አስቆጥሯል።
ምድብ ሁለት ሌላው የተደረገው ጨዋታ በካናዳ እና በኳታር መካከል ሲኾን ጨዋታው በካናዳ 6 ለ 0 የበላይነት ተጠናቅቋል።
በጨዋታው ላይ ሳይል ላሪን የመጀመሪያዋን ግብ ሲያስቆጥር፤ ጆናታን ዴቪድ ሀትትሪክ መሥራት ችሏል። ናታን ሳሊባ አምስተኛዋን ግብ ሲያስቆጥር፣ ሙሐመድ ማናይ በራሱ መረብ ላይ ስድስተኛዋን እና የመጨረሻዋን ግብ አስቆጥሯል።
በዚህ ጨዋታ የኳታር ሁለት ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል። ይህ ድል ካናዳን ወደ ቀጣዩ ጥሎ ማለፍ ደረጃ የማለፍ ዕድሏን አስፍቶላታል።
በምድብ አንድ ሁለተኛ ጨዋታ፣ አስተናጋጇ ሜክሲኮ ደቡብ ኮሪያን 1 ለ 0 በኾነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ የምድብ መሪነቷን አጠናክራለች።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ 0 ለ 0 በኾነ ውጤት ተጠናቅቆ ነበር። ይሁን እንጂ ከእረፍት መልስ በ50ኛው ደቂቃ ላይ ሌዊስ ሮሞ ለሜክሲኮ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ ለባለሜዳዎቹ ሦሥት ነጥብ አስገኝታለች።
ይህንን ውጤት ተከትሎ ሜክሲኮ ሁለተኛ ተከታታይ ድሏን በማስመዝገብ ወደ ቀጣዩ ጥሎ ማለፍ ደረጃ ለመሻገር አስተማማኝ ዕድል ፈጥራለች።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here