ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የጨዋታ መዘግየትን ለማስቀረት፣ ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማረጋገጥ እና የዳኝነት ውሳኔዎችን ይበልጥ ፍትሐዊ ለማድረግ በርካታ የሕግ ማሻሻያዎችን እያጠና መኾኑን ገልጿል።
በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ ተግባራዊ ሊኾኑ ይችላሉ የተባሉት ሕጎች:-
1. የእጅ ውርወራ የጊዜ ገደብ፦
አንድ ተጫዋች የእጅ ውርወራ በሚያደርግበት ወቅት ኾን ብሎ ጨዋታውን ለአምስት ሰከንድ ካዘገየ ውርወራው ተሰርዞ ለተቃራኒ ቡድን ይሰጣል።
2. የግብ ጠባቂዎች ሰዓት የማባከን ቁጥጥር ፦
ግብ ጠባቂዎች ከግብ ክልል ኳስ በሚመቱበት ወቅት ኾን ብለው ሰዓት ለመግደል ከሞከሩና ለአምስት ሰከንድ ኳስ ይዘው ከቆዩ ለተቃራኒ ቡድን ቀጥተኛ ያልኾነ የቅጣት ምት ወይም የማዕዘን ምት ሊሰጥ የሚችልበት አሠራር እየተጠና ነው።
3.የተቀያሪ ተጫዋቾችን የተመለከተ፦
በጨዋታ ላይ የተቀየረ ተጫዋች በ10 ሰከንድ ውስጥ ሜዳውን ለቆ መውጣት ይኖርበታል። ይህ ሳይኾን ቢቀር ግን የሚተካው አዲስ ተጫዋች ለአንድ ደቂቃ ያህል ወደ ሜዳ እንዳይገባ የመታገድ ቅጣት ይጠብቀዋል።
4. ከሜዳ ውጪ የሚደረግ የ60 ሰከንድ ሕክምና፦
በሕክምና ባለሙያ ሜዳ ውስጥ ሕክምና የተደረገለት ተጫዋች ኾን ተብሎ የሚደረግ የሰዓት ማባከንን ለመከላከል ሲባል ወደ ሜዳ ከመመለሱ በፊት ለ1 ደቂቃ ከሜዳ ውጭ መቆየት ይኖርበታል።
5. አፍን ሸፍኖ መነጋገር እና የቀይ ካርድ ጉዳይ፦
በተጫዋቾች መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ወቅት አፉን በእጁ ሸፍኖ የንቀት ወይም የዘረኝነት ስድብ የሚሳደብ ተጫዋችን በቀጥታ በቀይ ካርድ ለመቅጣት ሃሳቦች ቢነሱም ሕጉን በተግባር ለማዋል ግን የቪዲዮ ረዳት ዳኛ ምስልን እና ድምጽን የማዛመድ ጥብቅ ማረጋገጫ ስለሚፈልግ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ክርክር እየተደረገበት ይገኛል።
6. የማዕዘን ምት እና የቪዲዮ ረዳት ዳኛ ወይም ቫር ዳኞች፦
አጠራጣሪ የኾኑ የማዕዘን ምት ጥያቄዎችን ለመፍታት ቫርን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ መደረግ ያለበት ጨዋታው ሳይቀጥል በፊት እና ፈጣን በኾነ ሁኔታ ብቻ ነው።
7. የሁለተኛ ቢጫ ካርድ በቫር መፈተሽ፦
በሁለት ቢጫ ካርድ በቀይ ከሜዳ የሚባረሩ ተጫዋቾች፣ ሁለተኛው የተሰጣቸው ቢጫ ካርድ ስህተት መኾን አለመኾኑን በቪዲዮ ረዳት ዳኛ ቫር የመፈተሽ ዕድል ያገኛሉ ነው የተባለው።
ሕጎቾ ከመጽደቃቸው በፊት በተለያዩ የታችኞቹ ሊጎች እና የወጣቶች ውድድሮች ላይ በሙከራ ደረጃ እያዩዋቸው ይገኛሉ።
በተለይም የሰዓት ማባከንን መከላከል የፊፋ ዋነኛ ትኩረት በመኾኑ አንዳንዶቹ ሕጎች በ2026ቱ የአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ ላይ በከፊልም ቢኾን ተግባራዊ ሊኾኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !



