በዓለም የእግር ኳስ ታሪክ ትልቁን ዳኛ የማታለል ታሪካዊ ክስተት ሲታወስ።

0
5
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከ24 ዓመታት በፊት እ.አ.አ ሰኔ 3/2002 በዓለም ዋንጫ ታሪክ እጅግ አሳዛኝ እና አወዛጋቢ የተባለ የሜዳ ላይ” የማስመሰል ድራማ” ተከስቶ ነበር።
በ2002ቱ የኮሪያ/ጃፓን የዓለም ዋንጫ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ከቱርክ ጋር ባደረገው የምድብ መክፈቻ ጨዋታ ላይ የብራዚሉ ኮከብ ሪቫልዶ የማዕዘን ምት ለመምታት ወደ ማዕዘን በሚያመራበት ጊዜ ኳስ ከእግሩ ሥር የነበረው የቱርኩ ተከላካይ ሀካን ኡንሳል ኳሷን ወደ ሪቫልዶ አቅጣጫ ይመታታል።
የተመታችው ኳስ በትክክል ያረፈችው በሪቫልዶ ጉልበት ላይ ቢኾንም የባርሴሎና እና የብራዚሉ ኮከብ ሪቫልዶ ግን ፊቱን እንደተመታ አስመስሎ መሬት ላይ በመውደቅ በከፍተኛ ህመም ሲንከባለል ታይቷል።
በዚህ ድርጊት የታለሉት ደቡብ ኮሪያዊው ዋና ዳኛ ኪም ዮንግ ጆ ለቱርኩ ተከላካይ ሀካን ኡንሳል በቀጥታ ቀይ ካርድ በመስጠት ከሜዳ አሰናብተውታል።
ይሁን እንጂ ክስተቱ በቪዲዮ ታይቶ ከተመረመረ በኋላ ፊፋ ሪቫልዶን ጉዳት እንዳልደረሰበት እያወቀ “አስመስሎ በመውደቅ እና ዳኛን በማታለል” ጥፋተኛ አድርጎታል።
በዚህም የተነሳ ተጫዋቹ የ7 ሺህ 350 የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበት ነበር።
ብራዚል ጨዋታውን 2 ለ 1 ብታሸንፍም፣ ይህ የሪቫልዶ ድርጊት ግን በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ እስካሁን ድረስ ትልቁ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ማሳያ ተብሎ ይጠቀሳል።
ብራዚል ከቱርክ ግማሽ ፍጻሜ ላይ በድጋሚ ተገናኝተው ብራዚል 1ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜ ማለፏ ይታወሳል። በፍጻሜው ጨዋታም ጀርመንን 2 ለ 0 አሸንፋ ዋንጫውን አንስታም ነበር።
ከቀናት በኋላ በሦሥት የአሜሪካ ሀገሮች ጣምራ አዘጋጅነት በሚዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ብራዚል በምድብ ሦሥት ቱርክ ደግሞ በምድብ አራት ተደልድለዋል።
በጥበቡ ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here