በዳይመንድ ሊጉ ሁለተኛ መድረክ 🇪🇹 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዛሬ ይጠበቃሉ፡፡

0
36

 

ባሕር ዳር : ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2026 የዳይመንድ ሊግ አትሌቲክስ ውድድር ሁለተኛ መድረክ ዛሬ ይካሄዳል፡፡

ባለፈው ሳምንት በቻይናዋ ሻንጋይ ከተማ የተጀመረው የዓመቱ የዳይመንድ ሊግ ውድድር እዛው ቻይና ላይ ሁለተኛ መዳረሻ በኾነችው ዢያሚን ከተማ ዛሬ ይቀጥላል፡፡

የውድድሩ አዘጋጆች በዚሁ መድረክ በተለያዩ ርቀቶች የተወዳዳሪዎችን ዝርዝር ይፋ ያደረጉ ሲኾን በዚህም 7 ሴት እና 6 ወንድ በድምሩ 13 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተካትተዋል፡፡

ከነዚህም መካከል በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር ብርቄ ኃየሎም ለአሸናፊነት ቀዳሚ ግምት አግኝታለች፡፡ አትሌቷ ባለፈው ሳምንት የዳይመንድ ሊጉ መክፈቻም 3 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ ከ56 ማይክሮ ሰከንድ በኾነ ጊዜ በመግባት የውድድሩን ክብረ ወሰን በማሻሻል ማሸነፏ ይታወሳል፡፡

ከብርቄ ኃየሎም ጋር ወርቅነሽ መሠለ እና ሳሮን በርሄ አብረዋት ይሮጣሉ፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሠናክል ኬና ቱፋ፣ ዓለምናት ዋለ፣ ወሰኔ አሰፋ እና ፍሬሕይወት ገሠሠ ለአሸናፊነት ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

በወንዶች 5ሺህ ሜትር ከሚወዳደሩት ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ደግሞ ቢኒያም መሐሪ ለአሸናፊነት ቀዳሚ ግምት ያገኜ አትሌት ኾኗል፡፡

በ5 ሺህ ሜትር ርቀት የምንጊዜም የዓለማችን 15ኛው ፈጣኑ አትሌት የኾነው ቢኒያም መሐሪ 12 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ ከ93 ማይክሮ ሰከንድ የግሉ ምርጥ ሰዓት ባለቤት ነው፡፡

ከቢኒያም መሐሪ በተጨማሪ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ኩማ ግርማ፣ አዲሱ ይሁኔ፣ መዝገቡ ስሜ፣ ክሀይሪ በጂጋ እና አብዲሳ ፈይሳ ከሌሎች ሀገራት አትሌቶች ጋር ለአሸናፊነት ይፎካከራሉ፡፡

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_አትሌቲክስ #ኢትዮጵያ🇪🇹

በሀይሌ አበራ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here