ባሕር ዳር: ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ35ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ የመጨረሻ መርሐ ግብር ኤቨርተን የሊጉን የዋንጫ ተፎካካሪ ማንቸስተር ሲቲን በሜዳው ያስተናግዳል።
የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ የሁለት ቡድኖች ፉክክር ጎልቶ የታየበት ኾኗል። ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከፍተኛ ትንቅንቅ እያደረጉ ይገኛሉ።
ፉክክራቸውም ቀሪ ጨዋታዎችን ማሸነፍ እና በጎል በልጦ ዋንጫውን ማሸነፍ ኾኗል። ነጥብ መጣል ዋንጫን አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል። በተጨማሪም በእያንዳንዱ ጨዋታ በርካታ ጎሎችን ማስቆጠር የዋንጫ ባለቤቱን የሚወስን ይኾናል።
ከመሪው አርሰናል ሁለት ጨዋታዎችን ያነሰ የተጫወተው ማንቸስተር ሲቲ በ6 ነጥብ አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ዛሬ ከሜዳው ውጭ ተጉዞ ኤቨርተንን የሚገጥመው የፔፕ ጋርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ብቻም ሳይኾን የሊጉን ዋንጫ ላለማጣት ጨዋታውን ማሸነፍ ይኖርበታል።
የዴቪድ ሞይሱ ኤቨርተን በራሱ ሜዳ በሚያደርገው ጨዋታ ለትላልቅ ክለቦች ፈተና ኾኖ ታይቷል። ዛሬም ለማንቸስተር ሲቲ ፈታኝ እንደሚኾን ይጠበቃል።
በማንቸስተር ሲቲ በኩል ተከላካዮቹ ሩበን ዲያዝ እና ዮሽኮ ግቫርዲዮል በጉዳት አይሰለፉም።
በኤቨርተን በኩል ደግሞ ጃክ ግሪሊሽ እና ተከለካዩ ጃረድ ብራንዝዌይት በጉዳት የማይሰለፉ ናቸው። የፊት መስመር ተሰላፊው ቤቶ ለጨዋታው ዝግጁ መኾኑ ተረጋግጧል።
በዚህ ወሳኝ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ አሸንፎ ወደ አርሰናል ይጠጋል ወይንስ ኤቨርተን ለአርሰናል ውለታ ይውላል? የሚለው በደጋፊዎች ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል።
ጨዋታው ምሽት 4:00 ላይ በአዲሱ የኤቨርተን ሂል ዲክንሰንስ ስታዲየም ይደረጋል።
በሌላ ጨዋታ ቸልሲ ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር ይጫወታል። በደረጃ ሰንጠረዡ እየተንሸራተተ የሚገኘው ቸልሲ በአውሮፓ መድረክ ለመሳተፍ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ግድ ይለዋል። የመውረድ ስጋት ያለበት ኖቲንግሃም ፎረስት ለቸልሲ ፈታኝ እንደሚኾን ይጠበቃል። ጨዋታው ቀን 11:00 ይካሄዳል።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !



