ለፍጻሜ ከመድረስ ውጭ ዋንጫ ያላሳኩት የሁለት ክለቦች ፍልሚያ!

0
139
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ አርሰናል ከአትሌቲኮ ማድሪድ ዛሬ ይጫወታሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በሪያድ ኤር ሜትሮፖሊታኖ ባደረጉት የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ 1ለ1 በኾነ አቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወሳል።
አርሰናል በሜዳው ሲጫወት 60 ነጥብ 7 በመቶ የማሸነፍ ንጻሬ ያለው ሲኾን አትሌቲኮ በበኩሉ ከሜዳው ውጭ 16 ነጥብ 2 በመቶ የማሸነፍ ንጻሬ አለው ይህንን ተከትሎ አርሰናል የተሻለ የማሸነፍ ዕድል እንዳለው ይገመታል።
አርሰናል በአውሮፓ መድረክ ትልቅ ስም ቢኖረውም አንድ ጊዜ ለፍጻሜ ከመድረስ ውጭ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አሳክቶ አያውቅም።
በአንጻሩ በዲዮጎ ሲሞኒ የሚመራው አትሌቲኮ ማድሪድ በተደጋጋሚ ለፍጻሜ የደረሰ ነገር ግን ዋንጫ ማሳካት ያልቻለ ዕድለ ቢስ ቡድን በመኾን ይታወቃል።
የዛሬው የመልስ ጨዋታ ለሚካኤል አርቴታው ቡድን አርሰናል ከ20 ዓመታት በኋላ ለፍጻሜ ለመድረስ ብሎም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ለማሳካት የሚደረግ ጉዞ አካል ነው።
የሁለትዮሽ ዋንጫ ለማሳካት እየሠራ የሚገኘው አርሰናል በተለይ ምሽቱን በፕሪሚየር ሊጉ ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ የተለየ መነቃቃትን ይዞ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።
አትሌቲኮ ማድሪድ በበኩሉ ሦስት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሶ ዋንጫ ማንሳት አልቻለም። ዲዮጎ ሲሞኑ ዘንድሮም ክለቡን ለፍጻሜ ለማብቃት እና የዋንጫ ባለቤት ለማድረግ ትልቅ ተስፋ ይዘው አርሰናልን ይገጥማሉ።
ሁለቱም ቡድኖች በዚህ መድረክ ለፍጻሜ ከመድረስ ውጭ ዋንጫ ያላሳኩ በመኾናቸው ለፍጻሜ ለመድረስ ይፋለማሉ።
የዛሬው የጨዋታ አሸናፊ በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳ ፔስት ከፓሪስ ሴንት ጀርመን እና ባየርን ሙኒክ አሸናፊ ጋር በፍጻሜ የሚገናኙ ይኾናል።
ጨዋታው ምሽት 4:00 ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም ይደረጋል።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here