ፔኤስጂ ወይስ ባየርን ሙኒክ ?

0
57
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ፒኤስ ጂ ከባየርን ሙኒክ ዛሬ ምሽት ይጫወታሉ።
ሁለቱ ክለቦች በተገናኙባቸው ያለፉት 15 ጨዋታዎች ባየርን ሙኒክ ዘጠኙን በማሸነፍ የበላይነት አለው። ፔኤስጂ ደግሞ ስድስቱን አሸንፏል።
ባየርን ሙኒክ የዘንድሮን አንድ ጨዋታ ጨምሮ ያለፉትን አምስት ግንኙነቶች አሸንፏል። በአሠልጣኙ ቪንሰንት ኮምፓኒ ሥር አስደናቂ የብቃት ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየርን ሙኒክ በሩብ ፍጻሜው ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ ነው ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰው።
በሩብ ፍጻሜው ሊቨርፑልን ጥሎ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰው የባለፈው ዓመት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ፒኤስጂ ዛሬ ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል።
ፒኤስጅን እየመሩ በሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር 76 ጨዋታዎችን አድርገው 49 ያሸነፉት ሊውስ ኤነሪኬ የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፉ ከኾነ በመድረኩ በትንሽ ጨዋታዎች 50 ድሎችን የማሸነፍ ክብረ ወሰኑን ከፔፕ ጋርዲዮላ ይረከባሉ።
በዘንድሮው የሻንፒዮንስ ሊግ ጨዋታ እኩል 38 ግብ በተጋጣሚያቸው ላይ ያስቆጠሩት ሁለቱ ክለቦች የግብ ፉክክራቸው ዛሬም ተጠባቂ ነው።
በተጫዋች ጥራት አንቱ የተባሉት ሁለቱ ተፎካካሪዎች በተለይ በዛሬው ጨዋታ የፊት መስመራቸው በጉልህ ይጠበቃል።
በባየርን ሙኒክ በኩል ሀሪ ኬን፣ ሊውስ ዲያስ እና ሚኬል ኦሊሴ፤ በፒኤስጅ በኩል ደግሞ የባሎንዶር አሸናፊው ኦስማን ዴንበሌ፣ ዲሰሪ ዱዌ እና ክቫራስኬሊያ የሚያደርጉት ትንንቅ ይጠበቃል።
ከፒኤስጂ በኩል ጉዳት ላይ የቆዩት ቪትኒሃ እና ፋቢያን ሪውዝ ወደ ሜዳ እንደሚመለሱ ይጠበቃል። የአማካዮቹ ወደ ሜዳ መመለስ ለፒኤስጂ መልካም ዜና ነው።
ጨዋታው ምሽት 4:00 ላይ በፈረንሳይ ፓሪስ በፓርክ ዴ ፕሪንስ ስታዲየም ይካሄዳል። በምሽቱ ጨዋታ ማን ባለ ድል ይኾናል ? ባለሜዳው ፒኤስጂ ወይስ ባየርን ሙኒክ ? የምሽቱ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here