ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም እግር ኳስን የሚያስተዳድረው ፊፋ “በእግር ኳስ ውስጥ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ክልክል ነው ” ቢልም እውነታው ግን ያንን አያሳይም ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ፣ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ በሚያዘጋጁት የ2026ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ ከኢራን ይልቅ በውድድሩ የወደቀችው ጣሊያን ብትሳተፍ ማለታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው ። ምንም እንኳን የፕሬዝዳንቱ ሐሳብ በሁሉም ወገኖች ውድቅ ቢኾንም።
ታሪክን ወደኋላ ስንመለከት ፖለቲካ በእግር ኳሱ ውስጥ እንዳሻው መረማመዱን ልብ እንላለን፤ ለአብነት ያህል ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ (በ1950) ጀርመን በናዚ ታሪኳ ምክንያት ከዓለም ዋንጫው እንድትገለል ፖለቲካዊ ውሳኔ ተላልፎባታል።
በ1958 ኢንዶኔዥያ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከእስራኤል ጋር መጫወት አልፈለገችም። ምክንያቷ ደግሞ ከእስራኤል ጋር የነበራት ፖለቲካዊ ግንኙነት የሻከረ በመኾኑ ነው። በዚህም ምክንያት ኢንዶኔዥያ ከውድድሩ ተሰናብታለች።
በ1966 የዓለም ዋንጫም የአፍሪካ እና የእስያ ሀገራት ራሳቸውን ከውድድሩ አግልለዋል፤ የዚህም ምክንያቱ ፊፋ ለሁለቱ አሕጉራት የሰጠው ኮታ አነስተኛ በመኾኑ ነው ።
በ1970 አንዳንድ የአረብ ሀገራት ከእስራኤል ጋር መጫወት ባለመፈለጋቸው ምክንያት ራሳቸውን ከተሳትፎ አግልለዋል ።
በ1974ቱ የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ሀገራት እና የአፍሪካ ተወካዮች በዓለም ዋንጫው ላለመሳተፍ ውሳኔ አሳልፈዋል፤ ምክንያታቸው ደግሞ ደቡብ አፍሪካ በነጮች አገዛዝ (አፓርታይድ) ሥር ናት በማለታቸው ነው ። እንደ አብነትም ሞሮኮ እና ዛምቢያ በውድድሩ አለመሳተፋቸውን ማንሳት ይቻላል።
በ1994 ዩጎዝላቪያ በጦርነት ውስጥ ኾና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያገለላት ሀገር በመኾኗ በዓለም ዋንጫው ተሳትፎ እንዳይኖራት ፖለቲካዊ ውሳኔ ተላልፎባታል።
ቢቢሲ ስፖርት እንደዘገበው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት ምክንያት ከዓለም አትሌቲክስ ውድድሮችም ኾነ ከዓለም እግር ኳስ እንድትገለል ውሳኔ ተላልፎባታል።
ጉዳዩ ፖለቲካዊ ውሳኔ ስለመኾኑ ማስረጃው ደግሞ በጦርነቱ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ የኾነችው ዩክሬን ከየትኛውም ዓይነት ውድድር አለመታገዷ ነው። ሩሲያ ግን በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዳትሳተፍ መደረጓ ከአሜሪካ እና ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ፖለቲካዊ ግንኙነት ጥሩ ስላልኾነ ነው።
የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋቲኖ ደጋግመው ፖለቲካ በእግር ኳስ ውስጥ ጣልቃ አይገባም ቢሉንም እያየነው ያለው እውነታ ግን ፖለቲካ በእግር ኳስ ውሰጥ ያስገባው አንድ እግሩን ብቻ ሳይኾን ሁለቱንም መኾኑን ነው።
ዘጋቢ :- እሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !



