የአርሰናል ቀድሞ መቀደም ይደገም ይኾን?

0
95

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ታሪክ አራት ጨዋታዎች ብቻ እስኪቀሩ ድረስ ፕሪምዬር ሊጉን መርተው ዋንጫ ያጡ ክለቦች አሉ።

ኒውካስትል ዩናይትድ በ1995/96 የውድድር ዘመን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከነበረው ከማንቸስተር ዩናይትድ በ12 ነጥቦች በልጦ ሊጉን ይመራ ነበር። የነጥብ ልዩነት ቢጠብም እስከ 36ኛው ሳምንትም ሊጉን ይመራ ነበር፤ ነገር ግን በቀሪ ጨዋታዎች ነጥቦችን መጣሉን ተከትሎ ማንቸስተር ዩናይትድ ያልተጠበቀው ባለ ድል እንደነበር ይታወሳል።

ኒውካስትል ዩናይትድ የዚህ አሳማሚ ውጤት ባለታሪክ ነው። የወቅቱ አሠልጣኝ የነበሩት እንግሊዛዊው ኬቨን ኪገን ናቸው ።

አርሰናል በ2002/03 የውድድር ዘመን እስከ 30ኛው ሳምንት ድረስ ፕሪምዬር ሊጉን መርቶ ነበር፤ ነገር ግን በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች ወደ ኋላ ከመንሸራተቱም በላይ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም።

አርሰናል በዚያ የውድድር ዓመት ውጤት አፋፍ ላይ ደርሶ ሲንሸራተት ልማደኛው ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ከኋላው ተነስቶ ዋንጫውን ተረክቦ እንደነበርም የሚታወስ ነው። የወቅቱ የአርሰናል አሠልጣኝ አርሰን ቬንገር እና የማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ነበሩ።

እ.አ.አ በ2013/14 የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግም ሌላ አስገራሚ ውጤት ተመዝግቧል። ፕሪምዬር ሊጉ ሊጠናቀቅ አራት ጨዋታዎች እስኪቀሩት ድረስ ሊቨርፑል ሊጉን ሲመራ ነበር ።

ሊቨርፑል ከቼልሲ ጋር ያደረገውን የ35ኛ ሳምንት ጨዋታ የሊቨርፑሉ አምበል ስቴቨን ጄራርድ የሠራውን ስህተት በመጠቀም የዚያን ጊዜው የቼልሲ አጥቂ ዴምባ ባ በአግባቡ ወደ ግብነት ቀይሮ ሊቨርፑል በሁለት ለምንም ውጤት ተሸንፏል።

ይሄንን መልካም አጋጣሚ ሲጠብቁ የነበሩት ማንቸስተር ሲቲዎች ከሊቨርፑል ላይ መሪነቱን በመረከብ የዋንጫ ባለቤት መኾን ችለዋል። በወቅቱ ማኑኤል ፔሌግሪኒ የማንቸስተር ሲቲ ብሬንዳን ሮጀርስ ደግሞ የሊቨርፑል አሠልጣኞች ነበሩ።

እንደ ኦፕታ ያሉ የውድድር ውጤት ገማቾች የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግን አርሰናል ያሸንፋል ቢሉም ማንቸስተር ሲቲ ለዋንጫው እያደረገ ያለውን ፉክክር ወደ ላቀ ደረጃ አድርሶታል ።

ፕሪምዬር ሊጉ አምስት ጨዋታዎች እስኪቀሩት ድረስ ሊጉን ሲመራ የነበረው አርሰናል በ33ኛው ሳምንት በማንቸስተር ሲቲ በግብ ክፍያ ተበልጦ መሪነቱን ተነጥቆ ነበር።

አሁን ላይ አርሰናል ከማንቸስተር ሲቲ በአንድ ጨዋታ ብልጫ ወስዶ መሪነቱን በሦስት ነጥብ እና በአንድ የግብ ልዩነት እየመራ ይገኛል። አርሰናል ቅዳሜ ከፉልሃም ጋር የሚያደርገው ጨዋታም ማንቸስተር ሲቲ ሰኞ ምሽት ከኤቨርተን ጋር እስኪጫወት ድረስ ልዩነቱን ወደ ስድስት ነጥብ ለማሳደግ ዕድል ይፈጠርለታል ።

ዋናው ቁም ነገር ማንቸስተር ሲቲ ተስተካካይ ጨዋታዎችን አድርጎ አርሰናልን በመብለጥ የቀደሙ አስገራሚ ታሪኮችን ያሳየናል ወይስ አርሰናል ተፈትኖም ቢኾን ለብዙ ወራት የመራውን ፕሪምዬር ሊግ በድል ይቋጫል ? የሚለው ነው።

መልሱ በቀሪ ጨዋታዎች ይታወቃል።

ዘጋቢ :- እሱባለው ይርጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here