ባሕር ዳር: ሚያዚያ 10/2018 (አሚኮ) በ33ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በደረጃ ሠንጠረዥ ላይ እና ታች ጫፍ ላይ ያሉ ቡድኖች የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ለማጠናከር እና ወደ ሻምፕዮን ሽፑ ላለመውረድ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ።
የዕለቱ መርሐ ግብር በምዕራብ ለንደን ቀን 8:30 በሚደረገው የብሬንት ፎርድ እና ፉልሃም ፍልሚያ ተጀምሮ ምሽት 4:00 በዚያው ምዕራብ ለንደን በስታንፎርድ ብሪጅ ቸልሲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ ይጠናቀቃል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በ 55 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲኾን ከቸልሲ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፉ ለሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው ዋስትና ይኾነዋል። በሌላ በኩል ቼልሲ በ48 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጨዋታውን በማሸነፍ ወደ አውሮፓ መድረክ ተሳትፎ ለመጠጋት የሚጫወት በመኾኑ ጨዋታውን አጓጊ አድርጎታል።
በዚህ ጨዋታ የተጫዋቾች ጉዳት ለውጤቱ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይጠበቃል። በቸልሲ በኩል ወሳኝ ተጫዋቹ ሪስ ጀምስ በጉዳት ከጨዋታ ውጭ ሲኾን በማንቸስተር ዩናይትድ በኩል ደግሞ ሀሪ ማጓየር እና ሊሳንድሮ ማርትኔዝ በቅጣት አይሰለፉም። ሌኒ ዮሮ እና ማቲያስ ዴሊት በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው። የመሐል አማካዩ ኮቢ ሜይኑም የመሰለፍ ዕድሉ አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ይህም ለማንቸስተር ዩናይትድ ፈተና ይኾናል።
በሌላ የዛሬ መርሐ ግብር ቀን 11:00 ላይ ሊድስ ከወልቭስ የመኖር እና ያለመኖር ፍልሚያ ያደርጋሉ። ወልቭስ ከተሸነፈ የመውረዱ ነገር እርግጥ ለመኾን ይቃረባል። ኒውካስትል ከ በርንማውዝም በተመሳሳይ ሰዓት 11:00 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ምሽት 1:30 የሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶትንሀም ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት በሚያደርገው ጨዋታ ብራይተንን ያስተናግዳል።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !



