ቡና ባንክ ከታክስ በፊት ከ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዘገበ።

2

ቡና ባንክ አክሲዮን ማኅበር በ2025/26 የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት 3 ቢሊዮን 292 ሚሊየን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን ገልጿል።

የባንኩ የሀብት ማሠባሠብ ሥራ ውጤታማ እንዲኾን በደንበኞች እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው እምነት እና ተቀባይነት ወሳኝ ሚና መጫወቱን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሠብሣቢ ሙሉጌታ አስማረ ገልጸዋል።

ባንኩ 17ኛውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ባለአክሲዮኖቹ በተገኙበት አካሂዷል።

በጉባኤው የባንኩ የ2018 ዓ.ም. የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም እና የቀጣይ ዕቅዶች ቀርበዋል።

በዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት በ25 ነጥብ 9 በመቶ በማደግ 82 ቢሊዮን 557 ሚሊዮን ብር ደርሷል።

የተቀማጭ ገንዘቡ በ23 ነጥብ 3 በመቶ በማደግ 63 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ሲደርስ የብድር አቅርቦቱ ደግሞ በ24 ነጥብ 7 በመቶ በማደግ 53 ቢሊዮን 213 ሚሊዮን ብር መድረሱን ባንኩ አስታውቋል።

በተመሳሳይ የባንኩ ካፒታል በ28 በመቶ በማደግ 11 ቢሊዮን 287 ሚሊየን ብር ደርሷል።

የማይመለስ ብድር መጠንን የሚያመለክተው ሬሾም ወደ 4 ነጥብ 28 በመቶ መቀነሱን ገልጿል።

በዲጂታል ባንክ አገልግሎት ዘርፍ የሞባይል ባንክ ተጠቃሚዎችን ቁጥር በ64 ነጥብ 8 በመቶ፣ የኤጀንት ባንክ ተጠቃሚዎችን ደግሞ በ56 ነጥብ 9 በመቶ ማሳደጉን አመልክቷል።

ባንኩ በአጠቃላይ 444 ቅርንጫፎች ሲኖሩት፣ 305ቱ በአዲስ አበባ 139ኙ ደግሞ በክልሎች ይገኛሉ ተብሏል ።

በወርቅ ግዢ ዘርፍ 777 ሺህ 32 ግራም ወርቅ ከሕዝብ መሠብሠቡን የገለጸው ባንኩ፣ ከውጭ ምንዛሬ ምንጮች 197 ሚሊዮን 8 ሺህ ዶላር ገቢ ማግኘቱንም አስታውቋል።

በሰው ኀይል ልማት ረገድ 3 ሺህ 823 ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ባንኩ፣ በ142 የሥልጠና መርሐ ግብሮች 10 ሺህ 76 የሥልጠና ተሳትፎዎችን ማካሄዱን ገልጿል። በማኅበራዊ ኀላፊነት ሥራዎችም 18 ሚሊዮን 4ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን የቦርድ ሠብሣቢው አቶ ሙሉጌታ አስማረ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ልደታ እየተገነባ ያለው የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታም እስከ 15ኛ ወለል መድረሱን አስታውቋል።

አቶ ሙሉጌታ አስማረ እንደገለጹት፣ ቡና ባንክ እስከ 2029/30 የሒሳብ ዓመት ካፒታሉን ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ፣ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቱን ለማስፋት፣ አዳዲስ የገቢ ምንጮችን ለመፍጠር እና የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል ይሠራል ነው ያሉት።

በአየለ መስፍን

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#አዲስ_አበባ #ኅዳር_20_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየሀገሪቱን የሲሚንቶ ፍላጎት ግማሽ ያህሉን ብቻውን የሚሸፍነው ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ🇪🇹
Next articleዘመናዊነትን ከታሪካዊ ይዘት ጋር ያጣመረው የሀረር ኮሪደር ልማት ቱሪስት እየሳበ ነው።