
የሕጻናትን መብት እና ደኅንነት በተግባር ማረጋገጥ እንዲሁም ለተጋላጭ ሕጻናት ልዩ ትኩረት መስጠት የሁሉም አካላት የጋራ ኀላፊነት መኾኑ ተመላክቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን “ትኩረት እና እንክብካቤ ለሁሉም ሕጻናት” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የማጠቃለያ ዝግጅት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ ሕጻናት የዛሬዋ ሀገር ዜጎች በመኾናቸው በጤና፣ በአመጋገብ እና በትምህርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የሀገር አቅም ግንባታ መሠረት መኾኑን ገልጸዋል።
በግጭት እና በመፈናቀል የተጎዱ ሕጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ በመመለስ ረገድ ጠንክሮ መሠራት እንዳለበት አሳስበው፤ የበዓሉ ፋይዳ በሕጻናት ሕይወት ላይ በሚመጣ ተጨባጭ ለውጥ የሚለካ መኾኑን አስገንዝበዋል። አክለውም ለሕጻናት እኩል ዕድል መፍጠር፣ ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ እና ተሳትፏቸውን ማጠናከር ሁሉም ዜጋ ሊተገብራቸው የሚገቡ ቃል ኪዳኖች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ፤ በክልሉ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ እና ለጥቃት እንዲሁም ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የተጋለጡ ሕጻናት ቁጥር ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል።
ሕጻናትን ከኢኮኖሚ ብዝበዛ እና ከአደገኛ ሥራዎች ለመጠበቅ የሕግ ማዕቀፎችን እና ቅንጅታዊ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የጠቆሙት ኀላፊዋ እስከ ቀበሌ ባሉ መዋቅሮች ሕጻናትን ያሳተፉ የግንዛቤ ፈጠራ፣ የስፖርት ውድድሮች እና የፈጠራ ኤግዚቢሽን ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሕጻናት ፓርላማ አፈጉባኤ ሕጻን ቤተልሄም ኀይሉ ጎዳና ተዳዳሪ እና ወላጅ አልባ ሕጻናት እየተበራከቱ በመኾኑ ድምጽ ለሌላቸው ልጆች “ድምጽ” መኾን እንደሚገባ ገልጻለች። ሕጻናት የዛሬ ዓለም ውድ ሀብት በመኾናቸው እኩዮቿ ህልማቸውን በመመልከት በትምህርታቸው እንዲተጉም መክራለች።
በማጠቃለያ በዓሉ ላይ በሕጻናት የተሠሩ ልዩ ልዩ የፈጠራ ሥራዎች ጉብኝት ተካሂዷል።
ዘጋቢ፦ በቃሉ ፈረደ
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
