‎የጠላት ኀይል የኢትዮጵያን ድንበር ደፍሮ በክብር አይመለስም!

12

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው፣ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ጥልቅ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

‎የመከላከያ ሠራዊታችን ግንባታ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት የማይናወጥ ዋስትና ለመኾን ያለመ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።

‎በአካባቢው ችግር ሲከሰት የወንድም ሕዝቦች እና ሀገራት አለኝታ ለመኾን የሚያስችል ብቃት እየተገነባ መኾኑንም ገልጸዋል።

‎“እኛ የታጠቅነው ኢትዮጵያን እና ቀጣናውን አሁን ከሚታየው የተዘበራረቀ ሁኔታ ለመከላከል ነው፤ ማንንም የማጥቃት ፍላጎት የለንም፤ ይህንን ወዳጅም ኾነ ጠላት ሀገራት ሊገነዘቡት ይገባል” ነው ያሉት።

‎በምዕራብም ኾነ በምሥራቅ ያሉ ኀያላን ሀገራት የኢትዮጵያን ዝግጁነት በቅጡ ሊረዱት እንደሚገባ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ የሰላም አርበኝነት ዛሬ የተጀመረ ሳይኾን በደም እና በሕይወት የተጻፈ ታሪክ መኾኑን አስታውሰዋል።

‎በኮሪያ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን እና በሶማሌ ወንድሞች እና እህቶች ጎን ተሰልፎ የተከፈለው መሥዋዕትነት የዚህ ማሳያ ነውም ብለዋል።

‎የጥንካሬያችን ምንጭ ራስን የመከላከል አቅምን ከማጎልበት የዘለለ ሌላ ስውር አጀንዳ እንደሌለው ገልጸው የመከላከያ ሠራዊቱ አሁን የደረሰበት ቁመና እና ብቃት እጅግ የሚያኮራ መኾኑን ተናግረዋል።

‎ለጎረቤት ሀገራት እና ወንድሞች ስጋት ኾኖ ለመቅረብ ፍላጎት እንደሌለ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በታሪኳ የማንንም ሀገር ወራ እንደማታውቅ እና ወደፊትም የወረራ ፍላጎት እንደሌላት አስምረውበታል።

‎ኾኖም ማንኛውም የጠላት ኀይል ትንሽም ይሁን ትልቅ የኢትዮጵያን ድንበር ደፍሮ በወረራ ገብቶ በክብር የመመለስ ዕድል እንደሌለው አስጠንቅቀዋል።

‎ይህ ጽናት በመልክዓ ምድር አቀማመጥ ብቻ የሚለካ አለመኾኑን ጠቁመው ኢትዮጵያን ለመውረር የሚነሳ ማንኛውም አካል የአባቶቻችን የጀግንነት ታሪክ እንደሚጠብቀው ተናግረዋል “አትሞክሩን፤ ዓድዋ ይደገማል” ሲሉም በቁርጠኝነት ተናግረዋል።

‎ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

‎#የመደመር_መንግሥት!

‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!

‎#ባሕር_ዳር #ኅዳር_17_2019_ዓ_ም

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሻዕቢያ በማይታረም ስህተት ውስጥ የሚዳክር ኀይል ከኾነ ጥፋቱ ለኤርትራ ይኾናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article‎#አንኳር