
ሰልፍ ሄልፕ አፍሪካ በዲጂታል የማዳበሪያ ምክረ-ሐሳብ አገልግሎት፣ በድኅረ-ምርት ብክነት ቅነሳ እና በግብርና ኤክስቴንሽን አዋጅ ላይ ያተኮረ ከፍተኛ የፖሊሲ ውይይት መድረክ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን ክልሉ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምቹ የሥራ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል እና የምክር ቤት ማቋቋም ሥራዎችን አከናውኗል።
የክልሉ የ25 ዓመት የልማት ዕቅድ ዝቅተኛ ምርታማነትን ማሻሻል ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል። አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን አሳድገው ለገበያ እንዲያቀርቡ የመስኖ እና ፋይናንስ አቅርቦት ማነቆዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። በዚህ ዘርፍ ሰልፍ ሄልብ አፍሪካ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው የሲቪል ማኅበረሰቦችን ከፍተኛ የሰው ኀይል፣ ሀብት እና ዕውቀት ከመንግሥት ጋር በማቀናጀት መሥራት የልማት ዕቅዶችን በውጤታማነት ለመፈጸም ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ እና በቀጣናው ተሰሚነት ያላት መሪ እና አምራች ሀገር የማድረግ ኀላፊነት የአሁኑ ትውልድ ነው ብለዋል። ለዚህም የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ በዘመናዊ አሠራር ለመለወጥ እና ግብርናን ለማዘመን ተመራማሪዎች፣ ባለሙያዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምክክር እና በተግባር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የሰልፍ ሄልፕ አፍሪካ ካንትሪ ዳይሬክተር ድንቅነህ አስፋው ድርጅቱ በኢትዮጵያ የ40 ዓመታት የልማት ጉዞ ያለው መኾኑን ገልጸዋል። በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች አነስተኛ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በግብርና፣ በሥነ-ምግብ፣ በፀሐይ ኀይል በሚሠሩ የመስኖ እና የውኃ አቅርቦት ቴክኖሎጂዎች ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ድርጅቱ እ.ኤ.አ ከ2022 ጀምሮ በአማራ ክልል ከ100 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ አድርጓል። በኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ዩኒየኖች በኩል ተዘዋዋሪ ፈንድ በማመቻቸት የብድር እና ፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ አድርጓል። ድርቅን የሚቋቋሙ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብም ተጠቃሚ አድርጓል።
በሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ዋግኽምራ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በምርምር እና ቴክኖሎጂ የታገዘ የዲጂታል ማዳበሪያ አጠቃቀም ምክር አገልግሎት ማስተዋወቅ ተችሏል። የምርት ብክነትንም ለመከላከል በትኩረት እየሠራ ነው።
በአጠቃላይ ከመድረኩ የሚገኙ ምክረ-ሐሳቦችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ ተግባር በመለወጥ የአርሶ አደሮችን ምርታማነት እና የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራልም ብለዋል።
ስማቸው አጥናፍ
#SelfHelpAfrica #DigitalAgriculture #SmartFarming #FoodSecurity #Ameco
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
