
የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ በቃል ላይ የሰፈረ ዲፕሎማሲያዊ መዝገብ ብቻ አይደለም፤ የትውልድ ትውስታ፣ የታሪክ አሻራ እና የዕለት ተዕለት የኑሮ ሚዛን ጭምር ነው።
የአክሱም ሥልጣኔ ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ከነበሩ ታላላቅ እና ኀያላን ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያደረገ ታሪካዊ ክስተት መኾኑን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስ እና ሂዩማኒቲስ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ቴዎድሮስ ዘውዱ (ዶ.ር) አንስተዋል።
በተለይም በአዶሊስ ወደብ በኩል ከዓለም ጋር የሥልጣኔ፣ ጠንካራ የንግድ እና የዳበረ የባሕል ትስስር እንዲኖራት ማድረጉን ከአሚኮ ወቅታዊ ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
ሀገሪቱ የቀይ ባሕር ባለቤት በነበረችበት ዘመን የገነባችው የሥልጣኔ ማዕከል፣ የንግድ ትስስር እና የዲፕሎማሲ አቅም በዓለም ገናና እና ታሪካዊ እንድትኾን አድርጓት መቆየቱንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን የምታክል ታሪካዊ እና ገናና ሀገር ከቀይ ባሕር ርቃ እና ታጥራ እንድትኖር የተደረገው በ1980ዎቹ ዓ.ም ነው። ይህ ታሪካዊ መስተጓጎል የተከሰተውም በሕዝብ ፍላጎት ሳይኾን በወቅቱ በነበሩ የፖለቲካ መሪዎች እና በሻዕቢያ ሴራ መኾኑንም መምህሩ አመላክተዋል።
በዚሁ ሂደት ግብጽም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ ስትሠራ እንደነበር አስታውሰዋል። ግብጽ የዓባይ ወንዝን በብቸኛነት ተጠቃሚ ለመኾን ካላት ፍላጎት የተነሳ ኢትዮጵያ የቀጣናው ስጋት እንጂ የቀጣናው ደኅንነት አካል እንዳልኾነች አድርጋ በየጊዜው እንደምትከስም ጠቁመዋል።
በወቅቱ የግብጽ መሪ የነበረው ጀማል አብዱል ናስር ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖራት እና ከዓለም የፖለቲካ መድረክ እንድትርቅ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ሴራ ሲሠራ መቆየቱን አብራርተዋል።
ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ አሁን ላይ በታሪካዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ፣ በተፈጥሯዊ እና በሕጋዊ መንገዶች የባሕር በር ባለቤት የመኾን ሰፊ ዕድል እንዳላት እና የባሕር በሯን የማታገኝበት ምንም መሠረታዊ እና ሕጋዊ ምክንያት እንደሌለ በአጽንኦት ተናግረዋል።
የቀይ ባሕር ቀጣና ከሱዌዝ ካናል መከፈት ጀምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት የወጪ እና የገቢ ምርታቸውን የሚያንቀሳቅሱበት እጅግ ስትራቴጂካዊ ቀጣና መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነቷን እና ስትራቴጂካዊ ተጋላጭነቷን መቀነስ የምትችለው ታሪካዊ የባሕር በሯን በማስመለስ ብቻ ነው ብለዋል።
የዓለም የንግድ ቁሳቁስ በሚተላለፍበት በዚህ ወሳኝ ቀጣና ኢትዮጵያ ተዋናይ እንድትኾን ማድረግ ተገቢ ሲኾን ይህም በቀጣናው አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር እና የዓለምን ጥቅም ለማስከበር የላቀ ሚና እንድትጫወት ያስችላታል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ታሪካዊ የባሕር በሯን ተቀምታ ለወደብ ኪራይ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር አላግባብ ወጪ ማውጣቷ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ፈጥሮባታል።
ኢትዮጵያ ለጤና፣ ለትምህርት እና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች የሚውለውን እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኛውን ሕይወት ሊደጉም የሚችለውን የኢኮኖሚ አቅም ለወደብ ኪራይ ወጪ አላግባብ እያወጣች መኾኑን ዶክተር ቴዎድሮስ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንካራ እና ታታሪ ሠራተኛ ይሁን እንጅ አላግባብ የተጫነበት የወደብ ኪራይ ለኑሮ ውድነት ተጋላጭ እንዲኾን አድርጎታል።
130 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከሚመገቡት ምግብ ጀምሮ፣ ከሚከፍሉት የቤት ኪራይ እና ከሚጠቀሙት የትራንስፖርት አገልግሎት ድረስ ላልተገባ ክፍያ እና ለሞራል ኪሳራ መጋለጡንም አክለዋል።
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ያዳበረችውን ሰጥቶ የመቀበል ፖሊሲ እንደምታራምድ የጠቆሙት ዶክተር ቴዎድሮስ ከምዕራባውያን የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሁም ከአሜሪካ፣ ከእስራኤል እና ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ ቀይ ባሕር ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ የቀውስ ቀጣና መኾኑን አስገንዝበዋል።
ይህንን የቀውስ ቀጣና እንዲረጋጋ ከፍተኛ ቁጥር እና የሠለጠነ የሰው ኀይል ባለቤት የኾነችው ኢትዮጵያ ሚናዋ የላቀ መኾኑንም አብራርተዋል።
በመጨረሻም ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ የባሕር በር ይዞታዋ መመለሷ ለዓለም ሰላም እና ደኅንነት መረጋጋት ምንጭ ትኾናለች እንጂ ስጋት እንደማትኾን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
#የመደመር_መንግሥት!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
