የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትን ዕውን በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ ይገባል።

2

በዩኒቨርሲቲዎች ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ እና ከዚህም ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እንድታረጋግጥ በጥናት እና ምርምር፣ በዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እና በሰው ኀይል ልማት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

የባሕር በር አለመኖር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጫና እንዲሁም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በቀጣናዊ ትስስር ላይ የሚኖረውን ፋይዳ በመረጃ የተደገፈ ምርምር በማቅረብ ሊያሳዩም ይገባል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህራን እና ተማሪዎች ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ የባሕር በር ለኢኮኖሚ ፋይዳ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር እንድሪስ ሁሴን፣ የባሕር በር ለአንዲት ሀገር ኢኮኖሚ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም ይላሉ። በሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ የአንዲትን ሀገር ኢኮኖሚ ማነቃቃት አይቻልም የሚሉት መምህሩ የባሕር በር በምናስወጣቸው እና በምናስገባቸወ ምርቶች ይበልጥ ተጠቃሚ እንድንኾን ያደርጋል ነው ያሉት። ለዚህም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጥናት ላይ እና ዲፕሎማሲ ላይ መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ካሴ በበኩላቸው፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ትልቅ ሀገር፣ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ እና ለሎጂስቲክስ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ የምርት ዋጋ ንረትን እና የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን እንዴት እንደሚጎዳ በመረጃ አስደግፎ ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል።

በወሎ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር ቃሲም ይልማ ኢትዮጵያ የባሕር በር ሲኖራት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ይጨምራሉ፣ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ይሟላል። ይሄ ደግሞ ለኢኮኖሚው ትልቅ አስትዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የባሕር በር ማግኘት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ዋጋ በመቀነስ፣ የመጓጓዣ ጊዜን በማሳጠር እና የወደብ ኪራይ ወጪን በማስቀረት ለኢኮኖሚው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ተማሪዎች በበኩላቸው የባሕር በር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለውን ጠቀሜታ በሳይንሳዊ ጥናት፣ በዲፕሎማሲያዊ ትንታኔ እና በሕዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የማስረዳት ትልቅ ኀላፊነት ይጠበቅብናል ሲሉ ለአሚኮ ገልጸዋል።

✍️ ዘጋቢ:- ሳሙኤል ኪሮስ

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#ደሴ #ኅዳር_15_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከአፍሪካዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣሙ መፍትሔዎችን ማዘጋጀትና የመረጃ ደህንነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።