
የዓለም ሀገራት ከኋላ ቀር የጦር መሣሪያዎች በመውጣት በረቀቀ ቴክኖሎጂ የታገዙ፣ በርቀት የሚቆጣጠሩ እና ራሳቸውን ችለው ውሳኔ የሚሰጡ መሣሪያዎች ታጥቀዋል። የታጠቁት ቴክኖሎጂም የዘመናዊውን ውጊያ ስልት ሙሉ በሙሉ እየለወጠ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ የሌዘር መከላከያ ቴክኖሎጂዎች የዘመናዊውን የጦር ቴክኖሎጂ ገጽታ ቀይረዋል። ኢትዮጵያም የሀገር መከላከያ ሠራዊቷ የዘመኑን የጦር ቴክኖሎጂ በስፋት እንዲታጠቅ እየሠራች ነው። ከምድር እስከ ሰማይ፣ ከባሕር እስከ ሳይበር የሠለጠነ ሠራዊትን ገንብታለች።
የመከላከያ ሠራዊቷ በአየር ኀይል፣ በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ፣ በመከላከያ ኢንዱስትሪ፣ በድሮን ምርት፣ በወታደራዊ ምርምር እና ትምህርት፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በባሕር ኀይል የተጠናከረ እንዲኾን በመሥራት ላይ ናት።
የአውሮፕላን ጥገና፣ የመለዋወጫ እቃዎችን እና ድሮኖችን በራስ አቅም ማምረት ጀምሯል። ጀቶችን፣ የጦር አውሮፕላኖችን በመታጠቅ ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የበለጸ የአየር ኀይልን ገምብቷል። በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሎጂስቲክስ፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በአየር ላይ ዘመቻዎች እና በኤሌክትሮኒክስ ውጊያ ዘርፎች ውጤታማ ለመኾንም በትኩረት ተሠርቷል።
የባሕር ኀይልን ዳግም በማቋቋም የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅ ጥረት እያደረገ ነው። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የአራተኛ ትውልድ የጦር ቴክኖሎጂን በመታጠቅ ወደ አምስተኛ ትውልድ የጦር ቴክኖሎጂ እያተጓዘ መኾኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በመደመር መንግሥት ምስረታ ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የጸጥታ ተቋማት ይበልጥ እንዲዘምኑ እና እንዲጎለብቱ መሠራቱን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንገድ ምንጊዜም ሁለንተናዊ ኀይልን ማጠናከር ነው ብለዋል።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ራስን መቻል፣ ስትራቴጂያዊ የመከላከል ብቃትን ማሳደግ፣ የውስጥ ጥንካሬ የሚጸናበት ዘላቂነት ያለው መንገድ ማበጀት ላይ በትኩረት እንደሚሠራም አብራርተዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የጸጥታ አካላት ጥንካሬ አሁን ያለው ተልዕኮን የመፈጸም ብቃት የላቀ እንዲኾን መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ አየር ኀይል የአራተኛ ትውልድ የውጊያ አቅም መገንባቱን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የታጠቀቻቸው የጦር ቴክኖሎጂዎች ለቀጣናው ሰላም ዋስትና መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት የአፍሪካ ሀገራት በሚገጥማቸው ችግር ውስጥ ድንበር ተሻግሮ ሰላምን ለማስከበር የሚያስችል ብቃት ያለው አሥተማማኝ ሠራዊት ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
#የመደመር_መንግሥት!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
