
ለዘመናት የአፍሪካ የነጻነት ምልክት፣ የድል አድራጊነት ሠንደቅ የኾነችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ተደማጭ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ መኾኗን ቀጥላለች።
የአፍሪካ ኅብረት መሥራች እና የተባበሩት መንግሥታትን ከመሠረቱ ሀገራት መካከል የኾነችው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የአፍሪካውያን ማረፊያ፣ የዓለም አቀፍ ጉባኤዎች መዳረሻም ኾናለች።
ከራሷ አልፎ የአፍሪካ ሀገራትን በመሠብሠብ አህጉራዊ አንድነትን ለመፍጠር የምትሠራው ኢትዮጵያ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች” በሚለው መርህ ትታወቃለች።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማስተናገድ በጋራ ተጠቃሚነት የዲፕሎማሲ መርህ ከበርካታ ሀገራት ጠንካራ ግንኙነትን በመፍጠር የአፍሪካ ተምሳሌትነቷን እያስቀጠለች ነው።
የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ፣ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አሥፈጻሚ ምክር ቤት ሥብሠባ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጉባኤ፣ የኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት መድረኮች፣ የሰላም እና የደኅንነት ፎረሞች፣ ዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ኮንፈረንስ ብሎም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ታስተናግዳለች።
በቅርቡ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ለማስተናገድ ዝግጅት ጀምራለች። በርካታ የዓለም እና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ልማት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር እየመከሩ ነው። ኢትዮጵያ ዘመኑ የሚፈልገውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማሳለጥ የአፍሪካ መሪነቷን እያረጋገጠች ትገኛለች።
ንቁ ተሳትፎን ማረጋገጥ፣ አማራጭ የአጋርነት መስመሮችን ማስፋት፣ ከተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር በብልሃት መላመድ፣ መጓዝ እና ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ላይ የፊት አውራሪነት ሚና መውሰድ መንግሥት በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሚከተላቸው ወሳኝ መንገዶች ናቸው።
በዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በመሳተፍ እና በማዘጋጀት፣ ግንኙነትን በማጠናከር፣ የአፍሪካ ድምጽ በመኾን፣ በዘርፉ ውጤታማ ለመኾን እየሠራች፤ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት የኢኮኖሚ ዕድገቷን እያረጋገጠች ብሎም የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷንም እያሰፋች ነው።
ከኅዳር 14/2019 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ 5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የኅብረተሰብ ጤና ጉባኤ እያስተናገደች ትገኛለች። ለጉባኤው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ከተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ኀላፊዎች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷንም እያጠናከረች ነው።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ከተቀባይነት ወደ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማሸጋገር መሠራቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ወዳጆችን በማበራከት የሚተጋ፣ የደመኝነት ዕይታ ያላቸውን የሚመክር፣ ለቀጣናዊ ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ቅድሚያ የሚሰጥ እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
