
ዓባይ ባንክ እ.ኤ.አ በ2025/26 በጀት ዓመት ባከናወናቸው ስኬታማ የፋይናንስ አገልግሎቶች የ6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን ዛሬ እየተካሄደ በሚገኘው የባንኩ 17ኛ መደበኛ እና 9ኛ አስቸኳይ ድንገተኛ ጠቅላላ የባለአክስዮኖች ጉባኤ ላይ ይፋ አድርጓል።
ባንኩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባከናወናቸው ጤናማ የፋይናንስ ተግባራት እና በጥብቅ የፋይናንስ ሥነ-ሥርዓት በተመራ የወጪ አሥተዳደር ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ ከቀደመው እ.አ.አ 2024/25 የበጀት ዓመት አንጻር የ48 በመቶ ብልጫ በማሣየት የ6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ትርፍ አግኝቷል።
የተቀማጭ ገንዘብን በተመለከተ እ.ኤ.አ በ2025/26 በጀት ዓመት ባንኩ ፈታኝ ሀገራዊ እና ዓለም-አቀፋዊ የኢኮኖሚ ተጽዕኖዎችንበመቋቋም ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ያሳየውን ከፍተኛ የዕድገት ጉዞ አስቀጥሎ በዓመቱ አዲስ የተሠበሠበው አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 20 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲኾን ይህም አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ29 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ወደ 92 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር አሳድጓል።
የዓባይ ባንክ ጠቅላላ የብድር እና የቅድሚያ ክፍያዎችም ከ62 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።
ይህም ባንኩ ለሀገራዊ ዕድገት እየሠራ ሲኾን በማኅበረሰቡ ውስጥ የፋይናንስ አቅርቦት እና አካታችነት ላይ እየሠራ ይገኛል።
ከብድር ስርጭት ድርሻ አንጻር ለዓለም-አቀፍ ንግድ የቀረበው ፋይናንስ በ35 በመቶ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ሲኾን የኮንስትራክሽን እና የሕንፃ ዘርፍ በ20 በመቶ ድርሻ ይከተላል።
የሀገር ውስጥ ንግድ እና አገልግሎት የ14 በመቶ፣ የፍጆታ ብድር የ11 በመቶ፣ የትራንስፖርት እና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የ9 በመቶ እንዲሁም የአምራች እና ኢንዱስትሪ 8 በመቶ ድርሻ ይዘዋል። ቀሪው 3 በመቶ ለሌሎች ዘርፎች የተሰራጨ ብድር ነው።
ከዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ዕድገት ጋር በተያያዘም አጠቃላይ የዲጂታል ግብይቱን ወደ 70 በመቶ በማሳደግ የካርድ፣ የሞባይል እና የኢንተርኔት ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር 22 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት በማስመዝገብ በድምሩ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ተችሏል።
የዓባይ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሠብሣቢ ታደሠ አሰፋ በጉባኤው ላይ እንዳሉት የዓባይ ባንክ ዘላቂነት ያለው ዕድገት የተገነባው በጠንካራ የአፈጻጸም ልህቀት፣ በዲጂታል አሠራር ሽግግር፣ በደንበኛ ዕሴት ፈጠራ፣ በአገልግሎት ቅልጥፍና፣ በንቁ የሥጋት አሥተዳደር አመራር፣ በፋይናንስ አካታችነት እና በብሔራዊ ልማት አበርክቶ አድማስ መስፋት ብሎም በባለአክሲዮኖች ዘላቂ እና እያደገ የሚሄድ ድጋፍ ላይ ነው።
ባንኩ በ543 ቅርንጫፎች እና 9ሺህ 774 በሚጠጉ ትጉህ ሠራተኞቹ በመታገዝ 4 ነጥብ 45 ሚሊዮን ለሚኾኑ ደንበኞቹ ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ሐምሌ ዐ7/2002 ዓ.ም በ823 ባለአክሲዮኖች የተመሠረተው ዓባይ ባንክ አሁን ላይ ከ4ሺህ 700 በላይ ባለአክስዮኖች እና 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በመያዝ በሀገሪቱ የባንከ ኢንዱስትሪ ቀዳሚ ተዋናይ ከሚባሉት ውስጥ ገብቷል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#አዲስ_አበባ #ኅዳር_12_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
