አፍሪካ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን የመቋቋም አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ጉባኤ እያካሄደች ነው።

5

የመጀመሪያው ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች የአፍሪካ ቀጣናዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

“ከቃል ኪዳኖች ወደ አፍሪካ መር ተግባር፣ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን የጤና ደኅንነት፣ ሉዓላዊነት እና የመቋቋም አቅም ማሳደግ” በሚል መሪ መልዕክት ነው ጉባኤው እየተካሄደ የሚገኘው።

የአፍሪካ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታወች ኔትወርክ ፕሬዝዳንት ካውሹክ ራማያ በ2023 ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ለህልፈት ዳርገዋል ብለዋል።

ይህም በአህጉራችን ከሚከሰቱ ሕልፈቶች ውስጥ 45 በመቶውን ይይዛል፤ ይህም ከ1990 ጀምሮ በ45 በመቶ ጨምሯል ነው ያሉት።

በታኅሣሥ/2025 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታወችን እና በአዕምሮ ጤና ላይ ፖለቲካዊ ውሳኔ ማሳለፉን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ይህም 150 ሚሊዮን ያህል የትምባሆ ተጠቃሚዎችን መቀነስ፣ 150 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎች የደም ግፊታቸውን እንዲቆጣጠሩ ማድረግ እና 150 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎች የአዕምሮ ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻልን ያካትታል ብለዋል።

እንደ አህጉር አሁን ላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መኾን ያለበት እንደኾነም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል::

የኢትዮጵያ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታወች ጥምረት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ተቋማዊ መሠረቱን በማጠናከር፣ አጋርነትን በማስፋት እና ተላላፊ ባልኾኑ በሽታዎች ዙሪያ የሚደረገውን ቅስቀሳ በሀገር አቀፍ እና በቀጣና ደረጃ በማሳደግ አበረታች መሻሻል አሳይቷል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታወች ጥምረት ፕሬዝዳንት እና የጤና ሚኒስቴር አማካሪ ዶክተር አስቻለው ወርቁ ናቸው።

በኢትዮጵያም ኾነ በቀጣናው ለተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ጠንካራ፣ ይበልጥ የተቀናጀ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የኾነ የሲቪል ማኅበረሰብ ድምጽ ለመገንባት የሚደረጉ ትርጉም ያላቸው ሥራወችን እንሠራለን ብለዋል ዶክተር አስቻለው ወርቁ ።

በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልኾኑ በሽታወች እና የአ ዕምሮ ጤና ክፍል ኀላፊ ዶክተር ሰላማዊት አየለ እንደ ኢትዮጵያ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች 43 በመቶውን ሕልፈት እንደሚይዙ እና ከእነዚህም ውስጥ 27 በመቶው ከ40 ዓመት በታች የሚከሰቱ ያለጊዜያቸው የሚደርሱ ሞቶች መኾናቸውን በመድረኩ አንስተዋል::

አፍሪካ እንደ አህጉር ተላላፊ ያልኾኑ በሽታውች የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥታ መሥራት አለባት ብለዋል ዶክተር ሰላማዊት ::

ኢትዮጵያ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታወችን ለመከላከል የጤና ፖሊሲዋን እንዳሻሻለች ያነሱት ዶክተር ሰላማዊት የአልኮል መጠጦችን በሚዲያ ማስታወቂያ እንዳይነገር መከልከል፣ የማኅበረሰቡን የስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያግዙ የኮሪደር ልማቶች እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ ሥራወች ተላላፊ በሽታወችን ለመከላከል ከተሠሩ ተግባሮች መካከል መኾናቸውን አንስተዋል::

የዓለም ተላላፊ ያልኾኑ በሽታወች ጥምረት ሊቀመንበር ወይዘሮ ካቲ ዲየን በበኩላቸው እንደ ዓለም በየ ዓመቱ 45 ሚሊዮን ዜጎች ተላላፊ ባልኾኑ በሽታወች ሕይወታቸውን እንደሚያጡም አንስተዋል::

ለሁለት ቀናት ያህል በሚቆየው ጉባኤ ከ150 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ አካላት፣ ተላላፊ ካልኾኑ በሽታዎች ጋር የሚኖሩ ሰዎች፣ ወጣት መሪዎች፣ መንግሥታት እና አጋር አካላት ይሳተፉበታል::

✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!

#አዲስ_አበባ #ኅዳር_12_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የቀይ ባሕር ባለቤቶች” ፤ የባሕር በር ባለ እርስቶች!
Next articleዓባይ ባንክ ከታክስ በፊት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዘገበ።