
የመገጭ ግድብ ሐይቅ ወደ አሳ ልማት ተሸጋገረ።
🐬🐟 137 ሺህ የዓሣ ጫጩቶች ወደ ሐይቁ ተጨምረዋል
በርካታ ዓመታትን በትዕግሥት ጠብቆ የተጠናቀቀው የመገጭ ግድብ ለጎንደር ከተማ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ይዞ መጥቷል።
ጎንደር በዓሣ ልማት ውጤታማ እንድትኾን እገዛ ማድረግም ጀምሯል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ 137 ሺህ የዓሣ ጫጩቶችን በመገጭ ግድብ ላይ በመጨመር የዓሣ ምርትን ለማሳደግ ወደ ሥራ ገብቷል።
በመምሪያው የኤክስቴንሽን ኮምዩኒኬሽን ባለሙያ ሀብታሙ ዘገዬ የመገጭ ግድብን የዓሣ ምርት ማዕከል ለማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የተናገሩት። መገጭ ለጎንደር ከተማ የዓሣ ጸጋን አምጥቷልም ነው ያሉት።
ግድቡ ዓሣን የማልማት አቅሙ ከፍተኛ መኾኑን አንስተው በዓሣ ምርት ከ7 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በየአካባቢው የዓሣ ኩሬዎች ተዘጋጅተው እንዲለሙ መሠራቱንም ገልጸዋል። በየአካባቢው በተዘጋጁ ኩሬዎች ላይ 12 ሺህ የዓሣ ጫጩቶች መጨመራቸውንም ተናግረዋል።
የዓሣ ምርትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ዓሣ አስጋሪዎች በዘመናዊ መንገድ እንዲያሰግሩ እና የጥበቃ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንዲሠሩ ተደርጓልም ብለዋል።
የማቀነባበር፣ የክምችት እና የገበያ ትሥሥር መፍጠር ላይም ትኩረት ተደርጓል። የዓሣ ምርት ላይ ዘላቂነት እንዲኖር እና ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገር እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
ሕገወጥ የማስገር ተግባር እንዳይኖር ይሠራል ነው ያሉት። በዘርፉ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል። መምሪያው በ2018 በጀት ዓመት 87 ቶን የዓሣ ምርት ማግኘቱን ገልጸዋል።
በ2019 ሩብ ዓመት ከ97 ቶን በላይ የዓሣ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ 1ሺህ 213 ቶን የዓሣ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_11_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
