
የ2019 ዓ.ም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በመጪው እሑድ ኅዳር 13/2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የ2019 ዓ.ም የ10 ኪሎ ሜትር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ «ሩጫዬ ቀለሜ» በሚል መሪ መልዕክት በመጪው እሑድ በአዲስ አበባ እንደሚከናወን ተገልጿል። የዘንድሮው ውድድር ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር በመተባበር የሚካሄድ እንደኾነም ተጠቁሟል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ውድድር ከ55 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የነበሩ ሲኾን በዘንድሮው መርሐ ግብር የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 60 ሺህ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል ነው ያሉት።
ሚኒስትሯ ይህም ታላቁ ሩጫ እያደገ ተፈላጊነቱ እየሰፋ ሀገርን የማስተዋወቅ ግቡን እየመታ ይገኛል ብለዋል።
ላለፉት 26 ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስፖርታዊ ውድድር ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያውያን መለያ፣ የመዲናዋ ድምቀት እና ዜጎች ብዝኀነታቸውን እና ሀገራዊ አንድነታቸውን የሚያንጸባርቁበት ትልቅ መድረክ መኾኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
መንግሥት አዲስ አበባን የመዝናኛ፣ የባሕል እና የትልልቅ ኩነቶች ማዕከል ለማድረግ ባከናወናቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ከተማዋ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ለማስተናገድ ምቹ መኾኗን የጠቆሙት ሚኒስትሯ ውድድሩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ተሳታፊዎች የከተማዋን ሰፋፊ ጎዳናዎች፣ አደባባዮች እና ታሪካዊ ስፍራዎች እንዲጎበኙ ብሎም የሀገሪቱን ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ታላቁ ሩጫ በሀገር አቀፍ ደረጃ የስፖርት ንቅናቄን ከማጎልበት ባሻገር የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።
ከዚህ አጋርነት በተጨማሪም የቱሪዝም ሚኒስቴር «ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ» በሚል መርሐ ግብር በ6 ከተሞች ላይ በጋራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
በመጪው እሑድ የሚከናወነው የ10 ኪሎሜትር ታላቁ ሩጫ ላይ ተሳታፊዎች ሁሉ ሮጠው እንዲያጠናቅቁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
