‎ኮፕ 32 በስጦታ የተበረከተ ሳይኾን ኢትዮጵያ በላቧ ያስመዘገበችው የስኬት አክሊል ነው።

1

‎ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) በፈረንጆቹ 2027 በመዲናዋ አዲስ አበባ እንድታስተናግድ መመረጧ የዲፕሎማሲ ድል ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ባለፉት ዓመታት በዘመቻ ያከናወነችው የተግባር ስኬት ነው።

‎‎ይህ ታላቅ መድረክ በችሮታ ወይም በስጦታ የተበረከተ ሳይኾን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ላብ፣ በተግባር ሥራ እና በአርአያነት ያስመዘገቡት የስኬት አክሊል ኾኖ ተመዝግቧል።

‎‎ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በቃላት ሳይኾን በተግባር ለመመከት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ስትጀምር ዓለም በአድናቆት የተመለከተውን ታሪክ ጽፋለች።

‎‎በመርሐ ግብሩ የመጀመሪያ ዓመት በአንድ ጀምበር ብቻ ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የዓለምን ክብረ ወሰን የሰበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ በሰባት ዓመታት ውስጥ ከሰባት ቢሊዮን በላይ የሚጠጉ ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ ጉዞዋን አስቀጥላለች።

‎‎ያ! ጅማሮ በአንድ ዓመት ተገድቦ አልቀረም። ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል እና በመንከባከብ ከራሷ ድንበር አልፋ ለመላው ዓለም የአረንጓዴ ልማት ተምሳሌት መኾን ችላለች።

‎‎በዚህ ሂደትም የበርካታ ሀገራት መሪዎች እና ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ ችግኝ ተክለዋል፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገውን ተግባራዊ ምላሽ በአካል መስክረዋል።

‎‎የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጥቅሙ በወረቀት ላይ የሚጻፍ ብቻ ሳይኾን የአርሶ አደሩን እና የነዋሪውን ዕለታዊ ሕይወት በቀጥታ የሚነካ ነው። ይህ ግዙፍ የደን ልማት ሥራ የተራቆቱ ተራሮችን መልሶ በማልማት፣ የአፈር መሸርሸርን በመግታት፣ የከርሰ ምድር ውኃ እንዲጎለብት እና ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር ወሳኝ ፋይዳ አስገኝቷል።

‎‎ከዚህም ባለፈ የወንዞችን ፍሰት በማመጣጠን፣ ደለልን በመቀነስ እና የግድቦችን ዕድሜ በማራዘም ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ትልቅ ቀጣናዊ ትሩፋት ይዞ መጥቷል። ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሀገር በቀል ችግኞችን በስጦታ ማበርከቷም ቀጣናዊ የአየር ንብረት ትብብርን በተግባር ያጠናከረ ኾኗል።

‎‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን ለማስተናገድ የተመረጠችበት ስኬት ኢትዮጵያውያን በጋራ በሠሩት ሥራ የተገኘ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

‎‎ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የወሰደችው ተግባራዊ እርምጃ፣ የአረንጓዴ ልማት ባሕል እና በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነቡ የመሠረተ ልማት አቅሞች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አዲስ አበባን እንዲመርጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ነው ያሉት።

‎‎ጉባኤው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እና ለዓለም የምታቀርበውን ተጨባጭ መፍትሔ የምታሳይበት እንዲሁም የከተሞችን ገጽታ እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ የበለጠ የሚያነቃቃ መድረክ እንደሚኾንም ገልጸዋል።

‎‎የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር)፣ ኢትዮጵያ የ2027ቱን ኮፕ 32 እንድታስተናግድ የተወሰነው ውሳኔ የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ ተአማኒነት እና የአየር ንብረት ለውጥ መሪነት የሚያረጋግጥ መኾኑን አብራርተዋል።

‎‎ዓለም ስለ አየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ሲመክር ኢትዮጵያ መፍትሔውን ቀድማ በመሬት ላይ ሠርታ አሳይታለች። የ2027ቱ የኮፕ32 ጉባኤም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ ተጨባጭ የአረንጓዴ ልማት አስተዋጽኦ የሰጠው ፍትሐዊ ምላሽ ነው።

‎‎#የመደመር_መንግሥት!

‎‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

‎‎#ባሕር_ዳር #ኅዳር_11_2019_ዓ_ም

‎✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

‎‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous article‎ከንሥር የፈጠነ፣ ለጠላት ምትሀት የኾነ አየር ኀይል!