‎ከንሥር የፈጠነ፣ ለጠላት ምትሀት የኾነ አየር ኀይል!

4

‎በጥልቅ ምልከታው የጠላትን ዒላማ ነጥሎ ይመታል፣ ከዐይን ጥቅሻ የሚፈጥነው ጥቃቱ ጠላቶች ክብሯን ለመዳፈር እንዳያስቡ አድርጓቸዋል፣ ከንሥር በሚልቅ ፍጥነቱ ለጠላቶች ምትሀት ነው የኢትዮጵያ አየር ኀይል።

‎‎በዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂዎች፣ በብቁ ባለሙያዎች የተዋቀረው አየር ኀይል ጠላቶች የኢትዮጵያን የአየር ክልል ለመጣስ ቀርቶ ለማየት እንዳይደፍሩ አድርጓቸዋል።

‎‎ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስከበር ባሻገር የጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊነት፤ የግዛት አንድነት እንዳይደፈር፤ ምሥራቅ አፍሪካ የአሸባሪዎች ቀጣና እንዳይኾን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተወጥታለች፤ እየተወጣችም ነው።

‎‎አየር ኀይሉ በቴክኖሎጂ፤ በሰው ኀይል ሥልጠና እና የዝግጁነት አቅምን በማሳደግ የሀገሪቱ የአየር ክልል አይደፈሬ አድርጓል። ከትናንት እስከ ዛሬ በጸና አቋሙ፤ በከፍተኛ የውጊያ ብቃቱ እና በታሪካዊ የጀግንነት ገድሎቹ የሀገሪቱን ዳር ድንበር ከውጭ ጠላቶች እና ስጋቶች በጽናት በመከላከል ታሪካዊ ክብሩን አስቀጥሏል።

‎‎የኢትዮጵያ አየር ኀይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንዳሉት ጠንካራ የሰው ኀይል፤ ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ እና መሠረተ ልማት ካለ ማንም ሀገርን ሊዳፈር አይችልም ።

‎‎ኢትዮጵያ አሁን ላይ ጠንካራ የሳይበር ደኅንነት አቅምን በመገንባት፤ የላቁ ተዋጊ አውሮፕላኖችን፣ ድሮኖችን እና ዘመኑን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ ጠንካራ የአየር ኀይል ገንብታለች።

‎‎በተቋሙ ቴክኖሎጂን የማምረት፤ የመጠገን እና የመፈጸም አቅም አድጓል ብለዋል። ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ አቅም መፍጠርም ተችሏል። ለብሔራዊ ጥቅም የሚመጥን አቅም ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑንም ሌተናል ጄኔራል ይልማ አንስተዋል።

‎የአየር ኀይሉ የመፈጸም አቅም እያደገ በመምጣቱ የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያን ከመተንኮሳቸው በፊት ደጋግመው እንዲያስቡ አስገድዷቸዋልም ነው ያሉት።

‎‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) በቀጣናው የአየር ኀይል የበላይነትን ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ኢትዮጵያ እንደምትገነባ አረጋግጠዋል።

‎‎#የመደመር_መንግሥት!

‎‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

‎‎#ባሕር_ዳር #ኅዳር_11_2019_ዓ_ም

‎✍️ ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

‎‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous article‎የኢትዮጵያ መከላከያ የሕልውና አምድ፣ የሴራ ማክሸፊያ ምሽግ እና የሰላም ማማ!