
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ የታየው መነቃቃት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ገጽታ እየቀየረ ይገኛል።
በአንድ በኩል እንደ ጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት እና እንደ ሐረር ጀጎል ያሉ ነባር ቅርሶች በከፍተኛ ጥንቃቄ እድሳት ተደርጎላቸው ለጎብኚዎች ይበልጥ ምቹ እንዲኾኑ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከአዲስ አበባ የሸገር ፕሮጀክቶች (አንድነት፣ እንጦጦ እና ወዳጅነት ፓርኮች እንዲሁም የዓድዋ ድል መታሰቢያ) ጀምሮ በ”ገበታ ለሀገር” እና በ “ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች የተገነቡት እንደ ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት፣ ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት፣ ወንጪ፣ ኮይሻ፣ ጨበራ ጩርጩራ እና ሃላላ ኬላ ያሉ አዳዲስ እና ዘመናዊ የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻዎች መሠረተ ልማቶች የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ውበት ለዓለም ገበያ አቅርበዋል።
በግል ባለሀብቶች የተገነቡት እንደ ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት የመሰሉ ልማቶችም ለኢትዮጵያን ቱሪዝም ከፍታ ትልቅ ሚና አላቸው።
ይህ ሁለንተናዊ የልማት ሥራ ኢትዮጵያን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን የምትስብ ተመራጭ መዳረሻ ከማድረጉም ባለፈ ሀገሪቱ ከዘርፉ በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንድታገኝ አስችሏታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ቱሪዝም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከግብርና ጥገኝነት በማላቀቅ በፍጥነት ለማሳደግ የተመረጠ አንዱ እና ዋነኛው የኢኮኖሚ ምሰሶ መኾኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በታሪክ እና በባሕል የታደለች ብትኾንም ለዘመናት እነዚህን ሀብቶች አልምቶ ወደ ገንዘብ የመቀየር ክፍተት እንደነበር ጠቅሰዋል። አሁን እየተገነቡ ያሉ መዳረሻዎች ይህንን ታሪካዊ ስብራት እየጠገኑ የሚገኙም ናቸው።
የሚገነቡት የቱሪዝም መዳረሻዎች ለዛሬ ገቢ ማስገኛ ብቻ ሳይኾኑ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡ፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና ለመጪው ትውልድ የሚተላለፉ ዘላቂ ሀብቶች መኾናቸውን አጽንዖት ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ የቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የመዳረሻ ልማት ሥራዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የኾኑ አገልግሎቶች (ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች እና የመሠረተ ልማት አውታሮች) እንዲኖራቸው ማድረጋቸውን አስታውቋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደገለጸው የተሻሻለው የቪዛ አሰጣጥ ሥርዓት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ትስስር እና አዳዲሶቹ መዳረሻዎች ተደምረው የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ፍሰት ጨምሯል።
በ2018 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎችን በማስተናገድ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል። በኮንፍረንስ ቱሪዝም 220 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማዘጋጅት አዲስ እመርታ ተመዝግቧል።
#የመደመር_መንግሥት!
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
