ከተረጂነት ወደ አምራችነት የተሸጋገሩት የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች።

16

በከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ድጋፍ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ መኾን መቻላቸውን የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በከተማ ግብርና፣ በእንስሳት እርባታ እና በሌሎችም ዘርፎች ከ8 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውቋል።

ወይዘሮ እንደሻሽ ክፍሌ ለአሚኮ እንደገለጹት ባገኙት እገዛ በዶሮ እርባታ ተሰማርተው በሕይወታቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል።

ቀደም ሲል ልጆቻቸውን ለማስተማር እና የቤት ኪራይ ለመክፈል ይቸገሩ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ እንደሻሽ በአሁኑ ወቅት ከ750 በላይ ዶሮዎችን በማርባት እና የተሻለ የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ መኾናቸውን አብራርተዋል።

ሰፊ የመሥሪያ ቦታ እና ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ቢመቻችላቸው ሥራቸውን ይበልጥ በማስፋፋት ለሌሎች ዜጎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ አስተያየታቸውን ያጋሩት አቶ አበበ አለባቸው በበኩላቸው በማኅበር ተደራጅተው በከተማ ግብርና መሰማራታቸው ኑሯቸውን እንዳሻሻለላቸው ተናግረዋል።

በተሰማሩበት የበቆሎ ሰብል ልማት ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ የገለጹት አቶ አበበ በቀጣይ በንብ ማነብ እና በበጋ መስኖ ልማት ለመሰማራት ማቀዳቸውን ጠቁመው አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ባለሙያ ወርቅነሽ ዋለ ከድህነት ወለል በታች የነበሩ ዜጎችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እና የባሕርይ ለውጥ እንዲያመጡ የሚያስችል ሙያዊ እገዛ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዮሐንስ ካሴ እንደገለጹት የዜጎችን ዘላቂ ኑሮ ለማሻሻል የገቢ ማስገኛ ዘርፎችን በመለየት በክረምት የእርሻ ወቅት በበቆሎ ምርት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

ይህንኑ ተግባር በበጋው ወቅትም በመስኖ ልማት አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ አብራርተዋል። ጽሕፈት ቤቱ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ከመደገፍ ባለፈ ለመማር ማስተማር ሂደት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያግዙ የመማሪያ ክፍሎችን በከተማው ባሉ ትምህርት ቤቶች በመገንባት አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑንም ኀላፊው አክለዋል።

በዘርፉ የታቀፉ ተጠቃሚዎች የሚያነሱትን የመሥሪያ ቦታ እና የድጋፍ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠራም ተመላክቷል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ደብረ_ታቦር #ኅዳር_10_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፡ ተክለብርሃን ፈንታ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous articleአዲሱ ኮሪደር ልማት ምን ተገንብቶለታል?
Next article