
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ 4ኛ ዙር ጨዋታውን ከሞዛምቢክ ብሄራዊ ቡድን ጋር ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ያደርጋል።
ባሕር ዳር ዛሬ በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት አልባሳት በተዋቡ የዋልያዎቹ ደጋፊዎች አሸብርቃለች። የዋልያዎቹን መለያ የለበሱት ደጋፊዎች ከሩቅ የሚያስተጋባው የዝማሬ ድምጽ ለተጫዋቾች የኀይል ስንቅ ነው።
ባሕር ዳር የሀገር ፍቅር ስሜት በጉልህ የሚታይባት የድል አውድማ ኾናለች። የከተማዋ ጎዳናዎች በደስታ ማዕበል ተጥለቅልቀው የደጋፊዎችን ጥልቅ ፍቅር እና የማይበገር አጋርነት ሲመሰክሩ ውለዋል።
ከባሕር ዳር አልፎ ከመላው የኢትዮጵያ ማዕዘናት የተሠባሠቡት ደጋፊዎች ያሳዩት ወንዝ ተሻጋሪ ትስስር የብሔራዊ አንድነት እና የኅብረት ድንቅ ማሳያ ነው። ጾታን፣ ዕድሜን እና ማኅበራዊ ድርሻን በአንድ አቅጣጫ በማሰለፍ ለአንድ የጋራ ዓላማ የቆሙት እነዚህ ወገኖች፣ ስቴዲየሙን በጭብጨባ፣ በዜማ እና በሞቀ ማበረታቻ እያናወጡ ለዋልያዎቹ ከአሸናፊነት ውጭ ምርጫ እንደሌላቸው ይነግሯቸዋል።
የተጫዋቾች ዝግጁነት እና የድል ናፍቆትም ከደጋፊው ጉጉት ጋር ተናቦ ይታያል። የማፑቶውን ድል በመድገም እና በታሪክ አጋጣሚዎች ላይ አዲስ ምዕራፍ ለመጻፍ የተሰለፉት የዋልያዎቹ አባላት ሜዳ ላይ በሚያሳዩት ትግል የኢትዮጵያውያንን የረጅም ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የጥበቃ ዓላማ እውን ለማድረግ ቆርጠዋል።
ደጋፊውን በድል ለማስደሰት እና ሀገሪቱን ዳግም በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ ላይ ከፍ ለማድረግ ያላቸው ቁርጠኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የጎላ ነው። የዛሬው ቀን የኢትዮጵያውያን ስሜት በአንድነት ተጠርንፎ ድልን የሚሻበት፣ የዋልያዎቹ ዝና በድጋሚ የሚነበብበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
#AFCON_Qualifiers #EthiopiaVsMozambique #BDR-Stadium #AMECO
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
