
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት አርማ ናት፤ በማንም ቅኝ አልተገዛችም የሚለው ምስክርነት እንዲሁ በባዶ ቃላት የተገነባ አይደለም። ይልቁንም በአባቶቻችን ደም እና አጥንት የታተመ ፈጽሞ የማይፋቅ የክብር ታሪክ እንጂ።
አሜሪካዊ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሬይመንድ ጆናስ “ዓድዋ ኢትዮጵያን የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት እና የክብር ተምሳሌት አድርጓታል” ብለዋል።
የሶሺዮሎጂ እና የታሪክ ምሁር ዶናልድ ሌቪን በበኩላቸው “ታላቂቱ ኢትዮጵያ” በተሰኘው ሥራቸው የኢትዮጵያውያንን የነጻነት ወኔ እና የውጭ ጠላትን በጋራ የመመከት አስደናቂ የሥነ-ልቦና ጥንካሬ በስፋት አስረድተዋል። ያኔ በባዶ እግር በጋሻ እና ጦር ብቻ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀን ወራሪ ያንበረከከው ይኸው አልደፈርም ባይነት ከኢትዮጵያም አልፎ ለመላው አፍሪካ እና ለጭቁን የዓለም ሕዝብ የነጻነት ብርሃን ፈንጥቋል።
ይህ አኩሪ የጀግንነት ታሪክ የትላንት ትዝታ ብቻ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንዳስረዱት ያ የጥንቱ ጀግንነት እና የነጻነት ወኔ ዛሬም የጠፋ ሳይኾን በትውልዱ ደም ውስጥ ሰርጾ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ሕያው መንፈስ ነው።
አኩሪውን የማይካድ ሐቅ መረዳት የተሳናት እና ትላንት በጉንደት እና ጉራዕ በነበራት ቀጥተኛ ወረራ ያገኘችውን አሳፋሪ ሽንፈት የረሳችው ግብጽ ዛሬም በባንዳ ተላላኪዎቿ አማካኝነት ትንኮሳዋን አላቆመችም።
ኢትዮጵያ ጠል ታሪካዊ ጠላቶች ሊረዱት ያልቻሉት ትልቁ እውነት ቢኖር ኢትዮጵያዊነት የነጻነት ጽንስ መኾኑን ነው። ማንም የውጭ ኅይል በሴራም ኾነ በውክልና ጦርነት ይህንን የጸና ሀገራዊ ምሽግ ሊያፈርሰው ፈጽሞ አይችልም።
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከትላንቷ የምትለየው በውስጧ ያለውን ያን የነበልባልነት ወኔ በዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂ አዋህዳ አቅሟን አፈርጥማ መገንባቷ ላይ ነው።
ትላንት በባዶ እጅ በነበረው ሀገር ወዳድነት ብቻ የዓለምን የታሪክ ግስጋሴ ያስቀየረች ሀገር ዛሬ በውርስ ከተቀበለችው አሸናፊነት ባለፈ በረቀቀ የውጊያ ቴክኖሎጂ የታጠቀ እና በብቁ የሰው ኀይል የተደራጀ ዘመናዊ ሠራዊት ገንብታለች።
በሴራ እና በተላላኪዎቻቸው አማካኝነት ኢትዮጵያን ለመድፈር የሚቃጣቸው ኀይሎች ሁሉ ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ያ የድሮው የእሳትነት መንፈስ፣ ከዘመናዊው የብረት ክንድ ጋር የተዋሐደበት አስፈሪ ኀይል መኾኑን በጊዜ ሊገነዘቡት ይገባል።
#የመደመር_መንግሥት!
#EthiopiaPrevails #AfricanIndependence #AMECO
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
