
ለ2027 አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የኢትየጵያ ብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ጨዋታውን ዛሬ ቀን 10፡00 ያከናውናል፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ 4ኛ የምድብ ጨዋታ ዋልያዎቹ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዛሬ ከሞዛምቢክ አቻቸው ጋር ሲጫወቱ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ያላቸውን ዕድል ለማስፋት ነው፡፡
ከቀናት በፊት በምድብ 3ኛ ጨዋታቸው ማፑቶ ላይ ሞዛምቢክን በሜዳዋ በከነአን ማርክነህ ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 በማሸነፍ ወሳኝ ድል ይዘው የተመለሱት ዋልያዎቹ ይሄንን ተመሳሳይ ብሄራዊ ቡድን በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት ይገጥማሉ፡፡
3 ነጥብ ማግኘት ብቸኛ አማራጭ ለዋልያው በኾነው በዚህ ወሳኝ መርሐግብር የዋልያዎቹ አሠልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ 3 ነጥብ ለማግኘት እና ሕዝቡን ለማስደሰት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ከጨዋታው አስቀድሞ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በሜዳቸው ዋልያዎቹን ሲገጥሙ ያቀዱት እና ሜዳ ላይ የኾነው የተለየባቸው የሞዛምቢኩ አቻቸው አሠልጣኝ ቺኪንሆ ኮንዴ በበኩላቸው ጨዋታውን በብልጠት ድል አድርጎ ለመወጣት እንደሚሞክሩ በቅድመ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል፡፡
ትናንት ሴኔጋል ሱዳንን 4 ለ 2 በማሸነፍ የምድቡን መሪነት በ10 ነጥብ መያዟ አሁን ላይ የ2ኛነት የምድብ ቆይታን ለማረጋገጥ ፉክክሩ በዛሬ ተጋጣሚዎች ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ መካከል ኾኗል፡፡
ሞዛምቢክ በ4 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ዋልያዎቹ በ3 ነጥብ 4ኛ ላይ ናቸው፡፡ የዛሬ አሸናፊ ብሄራዊ ቡድንም ከሴኔጋል ቀጠሎ ለመቀመጥ እና 3ኛ ኾኖ ከምድብ ለማለፍ ዕድሉን የሚያሰፋበት ይኾናል፡፡
ይህ ወሳኝ ጨዋታም እንደተለመደው በደጋፊዎቹ ድባብ ታጅቦ ይከናወናል፡፡
ታዲያ ኢትዮጵያ የማፑቶ ድሏን ታስቀጥላለች ወይስ ቁጭት ያደረባቸው ሞዛምቢኮች ያሸንፋሉ ለሚለው ጥያቄ 10፡00 ላይ የሚካሄደው ጨዋታ ምላሽ ይሰጣል፡፡
ድል ለዋልያዎቹ!!!
በሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
