ብርድ እና ሐሩር የማይበግረው፣ ዳገት ቁልቁለት የማይገድበው የሉዓላዊነታችን ጋሻ!

14

ኢትዮጵያ ማለት ራሷን ችላ የቆመች፣ ነጻነቷን በልጆቿ ደም እና አጥንት ያጸናች፣ የባዕዳ እና የባንዳዎች ሴራ ያልበገራት የጀግኖች እልፍኝ ናት፤ መከላከያ ሠራዊታችን ደግሞ የዚህች ሀገር የሕይወት እስትንፋስ እና የመጨረሻው ምሽግ ነው።

እርሱ በአስተሳሰቡ የመጠቀ፣ በቴክኖሎጂ የላቀ፣ በሀገር ፍቅር ስሜት የተማረከ፣ በውጊያ ስልቱ የረቀቀ እና በወታደራዊ ሥነ ምግባር የታነጸ ነው።

ውርጩ እና ሐሩሩ፣ ብርድ እና ሙቀት አይበግረውም፤ ተራራ እና አቀበቱ፣ ቁልቁለቱ እና ዳገቱ አይገድበውም በየአውደ ውጊያው ከጠላት ጋር በመፋለም የኢትዮጵያን ታሪክ በድል አድራጊነት አስጠብቆ ኖሯል።

ድል አድራጊነት መገላጫው ነው፤ አልገዛም ባይነት ደግሞ መታወቂያው ነው። ዛሬ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት ኾኗል።

በሥነ-ልቦና እና በስትራቴጅካዊ ስልቱ ከቀደምት አባቶቹ የጀግንነት ቅብብል ጋር በማቀናጀት የሰላም እና የጸጥታ ግንብ ኾኖ ዘልቋል።

በእርግጥም ሠራዊቱ አጥንቱን ከስክሶ ሀገርን ያጸናል፤ ሕይወቱን ገብሮ ነጻነትን ያጎናጽፋል፤ የቁርጥ ቀን ጋሻ ነው። ባርነትን እና አልገዛምባይነትን አጥብቆ ያወግዛል፤ የባንዳ እና የባዕዳንን ተልዕኮ ጠንቅቆ የተረዳ ነው።

የውጭ ኀይሎች የጥፋት ዕቅድ እና የውስጥ ጸረ ሰላም ኀይሎችን የጥፋት አጀንዳ በየጊዜው ያመክናል።

በሰከነ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ግንዛቤ በመመራትም ሀገሩን ከከፋ አደጋ ጠብቋል።

በየአውደ ውጊያው የተጎናጸፈው ድል እና ጀብድ ዛሬ ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቷል፤ ስሙ በዓለም መድረክ የገነነው ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ በማውለብለብ ከፍተኛ ዝና እና ዕውቅና ተችሮታል፤ የኢትዮጵያን አይደፈሬነት እና አይበገሬነት ለዓለም በአደባባይ አስመስክሯል።

የኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን በድርሰታቸው ስለ ኢትዮጵያ ሠራዊት ጀግንነት፣ ጽናት እና መስዋዕትነት በስፋት ጽፈዋል።

ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በጣሊያን ወረራ ወቅት ራሳቸው በጦር ሜዳ ተሰልፈው የተዋጉ አርበኛ ነበሩ።

“ትዝታ” በተሰኘው (በታሪክ እና የሕይወት ገጠመኝ) መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት እና አርበኞች ዘመናዊ መሳሪያ ሳይኖራቸው በባዶ እግራቸው፣ ዳገት ቁልቁለቱን እና ረሃቡን ተቋቁመው በወኔ እና በሀገር ፍቅር ስሜት ብቻ የወራሪውን ጦር እንዳንበረከኩት በዐይን እማኝነት ጽፈዋል።

የባንዳዎችን ክህደት በማውገዝ የእውነተኛ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን የአልገዛም ባይነት ጽናት ዘክረዋል።

ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጦርነት” “አጤ ምኒልክ” እና “አጤ ቴዎድሮስ” በሚለው ታሪካዊ ድርሰታቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ኀይል በየዘመናቱ ከውጭ ወራሪዎች ጋር ያደረጋቸውን ተጋድሎዎች በዝርዝር አስፍረዋል።

ሠራዊቱ በአስቸጋሪ መልክአ ምድራዊ አቀማመጦች ውስጥ ኾኖ ጠላትን በረቀቀ የውጊያ ስልት ድል ማድረጉን፣ ሞትን የማይፈራ ቆራጥ መኾኑን እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በደሙ አጽንቶ ማቆየቱን ጽፈዋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጥንካሬው የሚመነጨው ከያዘው ብረት ብቻ ሳይኾን ለሀገሩ ክብር እና ለሰንደቅ ዓላማው ካለው ጥልቅ ፍቅር፣ ከአልገዛም ባይነት ሥነ-ልቦናው እና ሞትን ከማይፈራ ጽናቱ ነው።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_07_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየኢትዮጵያ አሸናፊነት እና የዘመኑ የሉዓላዊነት ምዕራፍ