
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ግብፅ ኢትዮጵያውያን የዓባይን ወንዝ አልምተው እንዳይጠቀሙ፣ ከድህነት እንዳይወጡ ለዘመናት ስታሴርና ሥትሠራ ኖራለች፤ አሁንም የባሕር በር ባለቤት እንዳትሆን ጥንተ ጠላትነቷን ቀጥላበታለች። የሕዳሴ ግድቡ እንዳይጀመር፣ ተጀምሮም እንዳይቋጭ እና ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን የመጠቀም ተፈጥሯዊ እና ሕጋዊ መብቷን ለማደናቀፍ ያልቆፈረችው ጉድጓድ የለም።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ደጅ በመጥናት ቀጣናዊ ውጥረቶችን እስከ መፍጠር የደረሱ የማደናቀፍ ጥረቶችን አድርጋለች። ይሄ ድርጊቷ የኢትዮጵያን አቅም በውል ካለመገንዘብ የመነጨ ስለነበርም አልተሳካላትም።
በብሔራዊ ጥቅማቸው የማይደራደሩት፤ በችግር ወቅት በአንድነታቸው የሚጸኑት ኢትዮጵያዊያንም የግብፅን የጠላትነት ድርጊት በመገንዘብ ግድባቸውን በሕብረብሔራዊ አንድነት አሳክተዋል። “ግድቡ የኔ ነው፤ ከግድቡ ወደ ወደቡ” በማለትም ለሌላ ከፍታ ጉዟቸውን ጀምረዋል። የግብፅ ሴራ በኢትዮጵያውያን አንድነት እና በመሪዎች ዲፕሎማሲያዊ ብስለት ሙሉ በሙሉ ተበጣጥሶ፣ ኢትዮጵያዊያን አንዱን ሕልማቸውን አሳክተው ሌላኛውን በሴራ ያጡትን ሀብታቸውን ለመመለስ ጉዟቸውን ቀጥለዋል። የጠላት ፈተና የማይበግራት ታላቋ ኢትዮጵያም ለጠላት አስፈሪ ክንዷን ማሳየቷን ቀጥላለች።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይኾን የቀጣናው የብልጽግና መሠረት በማድረግ የግብፅን “የስጋት ፕሮፖጋንዳና ሴራ” በተግባር አጋልጣለች። በትብብርና በጋራ የመልማት መርኋን ለሱዳን፣ ለኬንያ እና ለጅቡቲ የጉረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የቀጠናው አንከር መኾኗን ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ አስመስክራለች።
ኢትዮጵያዊያን ሲፈተኑ የሚበረቱ፣ ጠላት ሲነሳባቸው በአንድነት የሚሰባሰቡ፣ ለእናት ሀገራቸው ሳይሰስቱ ደማቸውን የሚያፈስሱና አጥንታቸውን የሚከሰክሱ መኾናቸውን መቸም የማትማረው ግብፅ በታሪኳ ኢትዮጵያን ለአፋታ እንኳን ሳትተኛ ለማዳከም ሠርታለች። የግብፅ ሴራ ያልበገራቸው ኢትዮጵያውያንም ያለማንም ድጋፍ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ሀሳብ እና ጊዜያቸውን ተጠቅመው ታላቁን የሕዳሴ ግድባቸውን እውን በማድረግ ታላቅነታቸውን በዓለም አደባባይ አንግሰዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ ከኃይል አቅርቦት ባለፈ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ አዲስ የጂኦ-ፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ግርማ ሞገስን ያላበሰ፤ የምሥራቅ አፍሪካ ዋነኛ የኃይል ማዕከል እንድትሆን ያደረገ ነው።
ጥንተ ጠላቷ ግብፅ አሁንም ከተለመደው የታሪክ ስህተቷ ባለመማር ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንዳትሆን ሴረዋን ቀጥላበታለች፤ ይሄ ድርጊቷ መቸም ተሳክቶላት ባያውቅም።
ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ የፍትሐዊነት ተጠቃሚነቷ፣ ተፈጥሯዊ እና ሕጋዊ መብቷን ለአፍታም ቢኾን ለድርድር እንዳላቀረበችው ሁሉ፣ የባሕር በር ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብቷንም ታስከብራለች። ቀጠናውን በልማት በማስተሳሰር በጋራ የመልማት ብሔራዊ ፍላጎቷንም አጠናክራ እየቀጠለች ነው።
#አሚኮ #የሕዳሴ_ግድብ #ኢትዮጵያ #GERD #Ethiopia 🇪🇹💪
የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_06_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
