
የአማራ ክልል የኢኮኖሚ ቁልፍ መሠረቶች ናቸው ኢንዱስትሪ እና ማዕድን። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተሰጣቸው ትኩረት የክልሉን የኢኮኖሚ ሞተር እያንቀሳቀሱ ነው። የዘርፉ ውጤታማነት የወጣቶችን ሕይወት እየቀየረ ነው።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ እና የማዕድን ቢሮ የክልሉን የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም በጥናት እና ምርምር በመደገፍ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ውጤታማ ለማድረግ እየሠሩ ነው።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ:-
ቢሮው በክልሉ 3 ሺህ 961 አዳዲስ ባለሀብቶች 553 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል እንዲያስመዘግቡ ሠርቷል። 174 መካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና 306 ሌሎች ፕሮጀክቶች ምርት እና አገልግሎት አስጀምሯል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 59 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 65 በመቶ ማሳደግ ችሏል። 583 አምራች ኢንዱስትሪዎች 789 ሺህ 948 ቶን ምርት በማምረት 1 ቢሊዮን 25 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማስቀረት ችለዋል።
ከ45 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና 6 የሆርቲካልቸር አልሚዎች 206 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር አስገኝተዋል። ከ100 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች (ከዚህ ውስጥ 83 ሺህ 243 ቋሚ) የሥራ ዕድል መፈጠሩን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የማዕድን ቢሮ:-
በአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባቀረቡት ሪፖርት በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም የማዕድን ልማት ቢሮ በብረት፣ በኢንዱስትሪ፣ በኮንስትራክሽን በማዕድን ፍለጋ እና ክምችት፣ በሕገወጥ ማዕድናት ቁጥጥር እና በሥነ ምኅዳር ጥናት ላይ በትኩረት ሠርቷል ብለዋል።
የብረት ክምች እና የፌሮ ብረት 146 ነጥብ 72 ሜትሪክ ቶን ብረት፣ 5 ሚሊዮን 148 ሺህ ቶን የብረት ማዕድን፣ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ቶን ግራናይት፣ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ቶን በላይ ጥቁር ድንጋይ እና ለአሲዳማ መሬት ማከሚያ የሚውል 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የኖራ ማዕድን ክምችቶች በጥናት መገኘታቸውንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ የመንግሥት ምሥረታ ላይ ባደረጉት ንግግር በኢኮኖሚ ጥንካሬ እና በሀብት ፈጠራ ላይ የምናስመዘግበው ውጤት፣ የምናረጋግጠው መዋቅራዊ ለውጥ ለሁሉም ሥራዎቻችን መፍትሔ ናቸው ብለዋል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በተጨባጭ ሀብት በሚፈጥሩ፣ የሕዝብን የኑሮ ደረጃ በሚያሻሽሉ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በዘመናዊ ግብርና፣ በማዕድን ሀብት ልማት፣ በቱሪዝም ሀብት፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች ላይ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
