
ኢትዮጵያ በታዳሽ ኀይል ልማት እያከናወነች ያለው ሰፊ ሥራ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ትልም እያፋጠነ እና ለቀጣናው ያላትን የኢነርጂ ማዕከልነት ሚና ከፍ እያደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሦሥት ወራት ብቻ ከ7 ሺህ 567 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኀይል ማመንጨት መቻሉን አስታውቋል። ይህም የሩብ ዓመት ዕቅድ 95 ነጥብ 1 በመቶ ነው።
የተገኘው አበረታች ውጤት ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ የኀይል ምንጮች የተገኘ መኾኑ የሀገሪቱን የአረንጓዴ ኢነርጂ ትኩረት ያሳያል።
ከዚህ ውስጥ 7 ሺህ 388 ነጥብ 17 ጊጋ ዋት ሰዓት (98 በመቶ) ከውኃ ሀብት የተገኘ ነው። ቀሪው 179 ነጥብ 49 ጊጋ ዋት ሰዓት (2 በመቶ) ደግሞ ከንፋስ ኀይል ማመንጫዎች የተገኘ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማመንጫ ጣቢያ ብቻውን ከ3 ሺህ 789 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ በማመንጨት 50 በመቶ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህም ለታዳሽ ኀይል እመርታ ትልቅ ምዕራፍ ኾኗል።
የጊቤ ሦሥት የኀይል ማመንጫ ጣቢያም 1 ሺህ 21 ጊጋ ዋት ሰዓት ኀይል አበርክቷል።
በሩብ ዓመቱ 17 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው የአይሻ 2 ንፋስ ኀይል ማመንጫ ሰባት ተርባይኖች ወደ ኦፕሬሽን በመግባታቸው ሀገራዊ የማመንጨት አቅምን ከ9 ሺህ 747 ሜጋ ዋት በላይ አድርሰውታል።
በሩብ ዓመቱ ከተመረተው ኀይል ውስጥ 91 ነጥብ 04 በመቶው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የቀረበ ነው። ቀሪው ለጎረቤት ሀገራት ሽያጭ የዋለ ነው። ይህም ሀገሪቱ ቀጣናውን በኢነርጂ ትስስር እንድታጠናክር ያግዛታል።
በቀጣይም አማካይ የኀይል ጭነትን በማሻሻል የኀይል ምርት ለማሳደግ እንደሚሠራም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል አስታውቋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#Ethiopia #EnergyHub #RegionalIntegration #EEP #Ameco
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_05_2019_ዓ_ም
✍️:- በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
