
ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን እና ብሔራዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ የሚቻለው በወታደሮች እና በመሣሪያዎች ብቻ ሳይኾን እነሱን ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ጠንካራ ተቋማት፣ ቴክኖሎጂ፣ የኢንዱስትሪ አቅም እና ቴክኖሎጂን የሚላመድ የሰው ኀይል ሲኖር ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዘመናዊ፣ ቴክኖሎጂን የተገነዘበ፣ በሀገር ውስጥ ምርት ራሱን የሚችል እና ሠራዊቱ ሙያዊ ብቃቱን የጠበቀ እንዲኾን እየተሠራ ይገኛል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሪፎርም ለውጥ ጉዞ በአየር ኀይል፣ በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ፣ በመከላከያ ኢንዱስትሪ፣ በድሮን ምርት፣ በወታደራዊ ምርምር እና ትምህርት፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በባሕር ኀይል የታጀበ ኾኗል።
ተቋሙ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሳይበር አቅም፣ በኤሌክትሮኒክስ ውጊያ እና በፍጥነት ውሳኔ የመስጠት ችሎታ ላይ የተመሠረተ እንዲኾን ተሠርቷል።
✍️ አየር ኀይል
ተቋሙ የአውሮፕላን ጥገና፣ ደረጃ ማሻሻል፣ የመለዋወጫ እቃዎች ምርት በራሱ አቅም ለማምረት እየሠራ ነው። ድሮኖችን፣ ጀቶችን፣ የጦር አውሮፕላኖችን በመታጠቅ ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የበለጸ የአየር ኀይልን እየገነባ ነው። አየር ኀይሉ 24 ሰዓት በጽናት የኢትዮጵያን አየር ክልሏን ይጠብቃል።
✍️የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር የሚያደርገውን ትብብር በሎጂስቲክስ፣ በሥልጠና፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በአየር ላይ ዘመቻዎች እና በኤሌክትሮኒክስ ውጊያ ዘርፎች ውጤታማ ለመኾን በጋራ እየሠራ ነው።
የተቋማቱ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የሀገር መከላከያ ሠራዊት መረጃ የሚሠበሥብበትን፣ የሚቀናብርበትን እና ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ ዘመናዊ ያደርጋል።
✍️የባሕር ኀይል ዳግም መቋቋሙ
ኢትዮጵያ ጠንካራ እና የዘመኑን የጦር ቴክኖሎጂ የታጠቀ ኀይል በመገንባት የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣና ደኅንነት ለማስጠበቅ እየሠራች ነው።
ዳግም የተቋቋመው የባሕር ኀይል ደግሞ ተጨማሪ የደኅንነት አቅም ለመኾን እየተዘጋጀ ነው። የምድር፣ የአየር፣ የሳይበር እና የባሕር ላይ አቅሞች ይበልጥ የአንድ ብሔራዊ የደኅንነት መዋቅር አካል እየኾኑ መጥተዋል።
ይህም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ግዳጅ የመፈጸም አቅም አሳድጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ድሮኖችን፣ ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን፣ ከባድ መሳሪያዎችን፣ መድፎችን እና ጥይቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም እየገነባች ነው ብለዋል።
አየር ኀይል የአራተኛ ትውልድ የውጊያ አቅም መገንባቱንም ገልጸዋል። የሀገሪቱን የውጊያ አውሮፕላኖች አቅም በእጥፍ ለማሳደግ መታቀዱንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የታጠቀቻቸው የጦር ቴክኖሎጂዎች ለቀጣናው ሰላም ዋስትና መኾናቸውንም ተናግረዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_05_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
