የስኳር ሕመም ቀድሞ ከታወቀ 80 በመቶ የሚኾነው ከሕመሙ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጠንቆችን መከላከል ይቻላል።

1

“የስኳር ሕመም ላይ ቀድመን እርምጃ እንውሰድ” በሚል መሪ ሀሳብ የዓለም የስኳር ሕመም ቀን ተከብሯል:: መርሐግብሩን በዓለም አቀፍ ደረጃም ኾነ በኢትዮጵያ ለ35ኛ ጊዜ ነው የተከበረው::

የኢትዮጵያ የስኳር ሕመም ማኅበር እና የጤና ሚኒስቴር በጋራ ባዘጋጁት መርሐግብር የኢትዮጵያ የስኳር ሕመም ማኀበር ከፍተኛ መሪዎች፣ አባላት፣ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የጤና ባለሙያዎች የተገኙ ሲኾን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበውበታል::

የኢትዮጵያ የስኳር ሕመም ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ በሰጡት ማብራሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ሕመም እየጨመረ መጥቷል፤ በቅርብ በተጠኑ ጥናቶች መሠረትም በኢትዮጵያ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከስኳር ሕመም ጋር ይኖራሉ ነው ያሉት።

80 በመቶ የሚኾነው የስኳር ሕመም ቀድሞ ከታወቀ ከሕመሙ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጠንቆችን መከላከል እንደሚቻልም አንስተዋል::

በዓሉ ኅዳር ወርን ሙሉ በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች ይከበራል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት፣ ነጻ ምርመራዎችን በማዳረስ እንዲሁም የስኳር ሕመምን ለመከላከል ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሥራዎች ይሠሩበታልም ብለዋል::

በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች እና የአዕምሮ ጤና ክፍል ኀላፊ ዶክተር ሰላማዊት አየለ በበኩላቸው እንደ ሀገር በማይተላለፉ በሽታዎች ሕይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥር ከፍ ያለ ነው፤ ማኅበረሰቡ ቀድሞ ምርመራ በማድረግ ራሱን እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል::

ከስኳር ሕመም ጋር በተገናኘ የምርመራ እና የመድኃኒት አቅርቦትን ለማዳረስም ከስኳር ሕመም ማኅበር እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር እየተሠራ ስለመኾኑ ዶክተር ሰላማዊት ተናግረዋል::

ቀኑ ሲከበር ግንዛቤ መፍጠር፣ ምርመራ ማድረግ እና የአኗኗር ዘይቤያችንን በመቀየር የስኳር ሕመምን ተጋላጭነት በመቀነስ ሊኾን እንደሚገባም በመርሐግብሩ ተመላክቷል::

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#አዲስ_አበባ #ኅዳር_05_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ቴዎድሮስ ኀይለኢየሱስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የምትመሰል ሀገር ኾናለች።