የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ለትውልድ እየተሸጋገረ መኾኑ የታየበት የዳካሩ የታዳጊዎች ድል!

3

4ኛው የዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር በሴኔጋል አስተናጋጅነት በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል።

በውድድሩ በአትሌቲክስ፣ በውሹ፣ በወርልድ ቴኳዋንዶ፣ በብስክሌት እና በውኃ ስፖርቶች የተሳተፈችው ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ አዲስ ታሪክ የጻፈችበትን እና ተስፋ የሰነቀችበትን አስደናቂ ድል በታዳጊ ስፖርተኞቿ አስመዝግባለች።

በአትሌቲክስ ውድድር 5 የወርቅ እና 3 የብር ሜዳሊያዎችን በድምሩ 8 ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ በዓለም የአትሌቲክስ ሜዳሊያ ሰንጠረዥ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ እንደቻለች ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ታዳጊ አንበሶቹ በዳካር አደባባይ የሀገራቸውን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ በማድረግ ታሪክ ሠርተዋል።

በወንዶች 800 ሜትር ወጣቱ አትሌት ዮሚፍ አበበ፤ በሴቶች 800 ሜትር ደግሞ አትሌት ነጻነት ሠለሞን ከበርካታ አትሌቶች ጋር እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ አድርገው የወርቅ ሜዳሊያውን ተቀዳጅተዋል።

በሌላ በኩል አትሌት ዋቢ ወጂራ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች እና በአትሌት ጁነዲን አብዶ በወንዶች 2ሺህ ሜትር መሰናክል፣ አትሌት ኤልሳቤጥ አማረ በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር በወርቅ ደምቀዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአትሌቲክሱ ዘርፍ በተለይም በመካከለኛ ርቀት ሩጫ የቀድሞ ጀግኖችን ፈለግ የሚተኩ ወጣቶች መጥፋት እንደ ሀገር በአትሌቲክሱ ዘርፍ በስጋት የሚነሳ ነበር።

በዳካር የተደረገው ውድድር የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ዝና የሚያስቀጥሉ ተተኪ ወጣት አትሌቶች ብቃት እና የወደፊት ተስፋ የሚያሳይ ታላቅ ስኬት የተመዘገበበት መኾኑንም ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

ታዳጊዎቹ ያስመዘገቡት ድል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በአስተማማኝ እጆች ላይ መኾኑንም ለዓለም ያሳዩበት ኾኗል።

በውድድሩ ታዳጊዎች ያስመዘገቡት ውጤት ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት ብቻ ሳይኾን በመካከለኛ እና በመሰናክል ውድድሮችም ወደፊት እየመጣች መኾኗን ያሳየችበትን ድንቅ ስኬት አስመዝግበዋል።

ውጤቱ የስፖርት ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲያነሱት ለነበረው የተተኪ አትሌቶች ስጋት ምላሽ የሰጠ ነው።

በዳካር ስኬታማ ውድድር አድርገው የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ ያደረጉት ታዳጊዎቹ በዋናው የኦሎምፒክ መድረክ የሀገራቸውን ክብር እንደሚያስጠብቁም ይታመናል።

ውጤቱ ተቀዛቅዞ ለነበረው የኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ የሞራል ስንቅ ኾኗል። በታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ ለሚገኙ የስፖርት አካዳሚዎችም ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

በቅርቡ በተለያዩ ሀገራት በተካሄዱ የጎዳና ላይ ሩጫ፣ የማራቶን እና የሀገር አቋራጭ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ታላላቅ አትሌቶች በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ ችለዋል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#Ameco #EthiopianAthletics #YouthOlympics #Dakar #Ethiopia

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_02_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየረጅም ጊዜ አብሮ የመሥራት ግንኙነትን ማስቀጠል ይገባል።