
አማራ ክልል በእንስሳት ሃብት ከፍተኛ አቅም አለው። በተለይም በዓሣ ሀብቱ ከትላልቅ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ሐይቆች እስከ ትናንሽ ኩሬዎች ድረስ ለዓሣ ምቹ የኾነ ትልቅ ጸጋ አለው።በባሕር ዳር ከተማ ደብረማርያም አካባቢ ነዋሪ አቶ ባሕሩ ሙሉዓለም በዓሣ ልማት ላይ ተሰማርተው
ይገኛሉ። ዓሣን ከጣና ሐይቅ ብቻ ሳይጠብቁ በጓሯቸው የነበረውን የጫት ማሳ በማጥፋት ዘመናዊ የዓሣ ኩሬ አዘጋጅተዋል። ከ2ሺህ በላይ ጫጩት አስገብተውም እያለሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በተመሳሳይ አቶ ውዱ ምርኩዝ በማኅበር ከ600 ካሬ ሜትር ላይ ዘመናዊ የዓሣ ኩሬ
ገንብተው ከ4ሺህ በላይ የዓሣ ጫጩቶችን እያለሙ እንደሚገኙ ነው የሚናገሩት። በቀጣይም የባለሙያዎችን ምክር በመከተል በስፋት እያለሙ ለመጠቀም ዕቅድ እንዳላቸው ሀሳባቸውን አጋርተውናል። የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሀብታሙ
ሁነኛው ለአሚኮ እንደተናገሩት የዓሣ ሀብት ልማትን ከእያንዳንዱ አርሶ እና አርብቶ አደር ማዕድ ጋር ለማስተሳሰር ዘመናዊ የዓሣ ኩሬዎችን የማስፋት እና ምርታማነቱን ለማሳደግ በስፋት እየተሠራ ነው:: አርሶ አደሮች በጓሮአቸው ዘመናዊ ኩሬዎች እያዘጋጁ የዓሣ እርባታን ከእርሻ
ልማቱ ጎን ለጎን እንዲያከናውኑ በማድረግ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ ታሳቢ ያደረገ ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል:: ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በመገጭ ግድብ ፕሮጄክት ምረቃ ወቅት “ግድቡን ለዓሣ ሀብት ልማት በማዋል የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ
ማድረግ እንደሚገባ” በሰጡት አቅጣጫ መሠረት የመገጭ ግድብን እና ሌሎች ግዙፍ የውኃ አካላትን ለዓሣ ሀብት ልማት በስፋት የመጠቀም ሥራ ተጀምሯል ነው ያሉት:: ለአብነትም በቅርቡ 125ሺህ የዓሣ ጫጩቶች ወደ መገጭ ግድብ መለቀቃቸውን አንስተዋል። የአካባቢውን ወጣቶችም
በማደራጀት ዘመናዊ የዓሣ ማጥመጃ መሳሪያዎችን የማመቻቸት ሥራ እንደሚሠራም ጠቁመዋል። በሌሎች ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ግድቦችም በተመሳሳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የቴክኖሎጂ አቅርቦትን በማጠናከር፣ ሥልጠናዎችን በማመቻቸት፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር የዘርፉን
ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት መኾኑንም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
