መሶብ – የዜጎችን ክብር የጠበቀ እና ቢሮክራሲን ያስቀረ የዲጂታል ምዕራፍ!

14
ለዘመናት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደጅ መጉላላት፣ የሰነድ አያያዝ መዛባት እና ከሰዓታት እስከ ቀናት የሚባክን ውድ ጊዜ የዜጎች የዕለት ተዕለት ሸክም ኾኖ ቆይቷል። ዛሬ ግን ይህ የድካም አዙሪት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ በአዲስ ተስፋ እየተቀየረ ይገኛል።
“መሶብ” በሚል ውብ እና ሀገራዊ መጠሪያ የተሰየመው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥርዓት የሕዝብን እንግልት በማስቀረት ረገድ ታሪካዊ እጥፋት እየፈጠረ ነው።
ተገልጋዮች የተለያዩ መብቶችን እና አገልግሎቶችን ለማግኘት ከቢሮ ወደ ቢሮ የሚንከራተቱበት ዘመን እንዲያከትም ይህ ማዕከል አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በአንድ የዲጂታል ጣሪያ ሥር አጣምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዩ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ እንዳሰመሩበት «መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለሙስና እና ለእንግልት የሚዳርጉ አሠራሮችን ሥር ነቀል በኾነ መንገድ የሚቀይር ነው»
ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመኾኑ ባለጉዳዩ አገልግሎቱን አግኝቶ እስኪወጣ ድረስ በሲስተም የሚመዘገብ እና ቁጥጥር የሚደረግበት ነው። ይህ ደግሞ በባለድርሻ አካላት መካከል ፍጹም ግልጽነትን እና አስተማማኝ ተጠያቂነትን አሰፍኗል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል በነበሩ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ውስንነቶች ምክንያት ዜጎች ለከፍተኛ ወጭ እና እንግልት ተጋልጠው ነበር። ታዲያ መንግሥት ይህንን የዕለት ተዕለት ሥቃይ ለማስቆም በባሕር ዳር፣ በደሴ፣ በጎንደር፣ በደብረብርሃን እና ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች “መሶብ የአንድ ማዕከልን ” ወደ ሥራ አስገብቷል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንችአምላክ ገብረማርያም እንደገለጹት ባለፈው ዓመት ብቻ በክልሉ በሚገኙ ማዕከላት ከ200 ሺህ በላይ ደንበኞች ፈጣን፣ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት ችለዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የኅብረተሰቡ እርካታ ከ99 በመቶ በላይ መድረሱ የለውጡን አወንታዊ ሂደት በግልጽ ያሳያል ነው ያሉት።
“ሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት” ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተመቻቸ እና ሰብዓዊነት የተላበሰ አሠራርም ነው።
አሁን ላይ በክልሉ 8 ማዕከላት ግንባታቸው ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሰጡ ሲኾን ይህ የልማት ምዕራፍ በሂደት እየሰፋም መጥቷል።
በበጀት ዓመቱም 10 አዳዲስ ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ እየኾኑ ይገኛሉ።
በተያዘው 2019 በጀት ዓመት ደግሞ ማዕከላቱን እስከ ወረዳ ደረጃ በማስፋፋት የመንግሥት አገልግሎት ተደራሽነትን እና ጥራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ኀላፊዋ ጠቁመዋል።
የ«መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት የቴክኖሎጂ አብዮት ብቻ ሳይኾን ለሰው ልጅ ክብር፣ ለዕውቀት እና ለቅልጥፍና የሰጠው የትኩረት ማረጋገጫ ነው። ለቀጣይ የሀገራችን የልማት ጉዞዎችም ትልቅ አርዓያ እና የኩራት ምንጭ ነው።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ምድራዊ ፈተና በዝቶ፣ ዙሪያው ቢነድ በገሞራ፤ ጥሰን እናልፈዋለን፣ የማይሞት ታሪክ ልንሠራ።” የወታደሩ ዝማሬ
Next articleለኅብረተሰቡ ትልቅ እፎይታ የሰጠው የአማራ ክልል የከተማ አውቶብሶች ስምሪት እና የኮሪደር ልማት!