
የቀድሞዋ መንቆረር፣ የአሁኗ ደብረ ማርቆስ ከተማ ከረጅም ዘመናት ጥያቄ በኋላ የአውሮፕላን ትራንስፖርት ተጠቃሚ መኾኗ የሚታወስ ነው። የአውሮፕላን ትራንስፖርት ከጀመረ በኋላ ከተማዋ በሁሉም ዘርፍ እየተነቃቃች በለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች። በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኙ
የሆቴል ሥራ አሥኪያጆች ለአሚኮ እንደተናገሩት በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ወደ አካባቢው ሳይመጡ የቆዩ እንግዶች በስፋት መምጣት መጀመራቸውን ተናግረዋል። የተለያዩ ስብሰባዎችም መካሄድ እንደጀመሩ ነው የገለጹት። በዚህ የተነቃቁት ሆቴሎችም አገልግሎታቸውን እያሳደጉ፣
እያዘመኑ እና የሠራተኞቻቸውን ቁጥርም እየጨመሩ እንደሚገኙ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መልካሙ ሽባባው የአውሮፕላን ማረፊያው ሥራ ከጀመረ በኋላ የከተማዋን እንቅስቃሴ እያነቃቃት እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተለይም
ማኅበረሰቡ ሳይንገላታ የሚፈልገውን የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሏል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ከአካባቢው ወደተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ የሚፈልገውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መሥተጋብሮችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።
የከተማዋ ንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ መነቃቃቱንም አንስተዋል። ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የማልማት ፍላጎት እና የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች በእጥፍ መጨመራቸውንም አብራርተዋል። ተጀምረው የነበሩት የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶችም በአዲስ
ተስፋ ተነቃቅተው ወደ ሥራ እየገቡ፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እየተፈጠሩ እንደሚገኙ ነው የገለጹት። ከተማዋ ተጨማሪ ገቢ እንድታገኝም አስችሏታል ብለዋል። የአውሮፕላን ማረፊያው ከተጀመረ በኋላ ከ155 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንድታገኝ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ነው ያሉት።
ከተማዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ትልቅ አቅም እንዳላት ገልጸው አሁን ላይ በርካታ ስብሰባዎችን እያስተናገደች፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እየተነቃቃ እና የጎብኝዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል። ከተማዋ ብዙ ጸጋዎች እንዳሏት የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከአገልግሎት
አሠጣጥ ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል። ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የቦታ አቅርቦት እና የዝግጅት ሥራዎች ተሠርተው ባለሃብቶችን እየጠበቁ እንደሚገኙም አመላክተዋል። ይህንን ተገንዝበው በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ የሚገኙ
ባለሃብቶች መጥተው በሚፈልጉት የኢንቨስትመንት መስክ ተሠማርተው በከተማዋ እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
