በአማራ ክልል ሀሰተኛ ደረሰኝን የሚያስቀር ምስጢራዊ የደረሰኝ ሕትመት ተጀመረ።

13

የዓባይ ሕትመት እና የወረቀት ፓኬጅንግ ፋብሪካ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የላቀ የደኅንነት ማተሚያ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኪውአር ኮድ (QR Code) የታገዘ ሚስጢራዊ የደረሰኝ ሕትመት አገልግሎት የማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ዘመናዊ የታክስ ደረሰኝ ሕትመት በክልሉም ኾነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የደረሰኝ አጠቃቀም ክፍተቶችን በመቅረፍ የገቢ ተቋማትን የገቢ አሠባሠብ ውጤታማነት ከፍ በማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተነስቷል።

የዓባይ ሕትመት እና የወረቀት ፓኬጅንግ ፋብሪካ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ታደሰ መላሽ የኪውአር ኮድ ደረሰኝ ሕትመት የደረሰኞችን ሕጋዊነት ያረጋግጣል ብለዋል። የመንግሥትን የግብር ገቢ የሚያሳድግ እና ማኅበረሰቡ ትክክለኛ ደረሰኝ እንዲያገኝ የሚያስችል መኾኑንም ተናግረዋል።

መጀመሪያ የታተመ ደረሰኝ ድጋሜ እንዳይታተም የሚቆጣጠር የዲጂታል ሥርዓት መልማቱንም ገልጸዋል። ደንበኞች ያዘዙትን ደረሰኝ የሚከታተሉበት እና ሕትመቱ ሲጨርስ መጥተው መውሰድ የሚችሉበት የዲጂታል ሥርዓት መኖሩንም አንስተዋል።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የዓባይ ሕትመት የወረቀት ፓኬጅንግ ፋብሪካ ምክትል የቦርድ ሠብሣቢ እና የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መላኩ ፈንታ ምስጢራዊ ደረሰኝን የኢንቨስትመንት አካል ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ፈንታው የኪውአር ኮድ ምስጢራዊ ደረሰኝ መታተሙ ደረሰኝን የማጭበርበር ሕገወጥ ተግባር የሚያስቀር ነው ብለዋል።

ተመሳስለው የሚሠሩ ደረሰኞች መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ገቢ ሲያስቀሩ እንደነበር አንስተዋል። ምስጢራዊ ደረሰኙ ይህንን ችግር ይቀርፋል ነው ያሉት። የምስጢራዊ ደረሰኝ ሕትመት በክልሉ መጀመሩ ሕገወጥ ተግባራትን የሚያስቀር መኾኑንም ተናግረዋል።

በገቢዎች ሚኒስቴር የባሕርዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ካሳሁን ደመመ የምስጢራዊ ደረሰኝ ሕትመት ለገቢ አሠባሠብ ሥርዓት ሂደት ውጤታማ ተግባርን የሚያመጣ ነው ብለዋል። ሀገርን ወደ ዕድገት ለማሻገር የሚያግዝ መኾኑንም ተናግረዋል። ሕጋዊነትን እንደሚያረጋግጥም ገልጸዋል።

ሀሰተኛ ደረሰኝ ሀገርን ያጠፋል፣ ታማኝ ግብር ከፋዮችን ይጎዳልም ብለዋል።

ዛሬ ወደ ሥራ የገባው የማተሚያ ማሽን በ24 ስዓት ውስጥ 4 ሺህ 200 ደረሰኝ እንደሚያመርትም ተገልጿል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_19_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየደብረ ታቦር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በሕዳር 2019ዓ.ም ሥራ ይጀምራል።
Next articleበአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ 67 የመስኖ ፕሮጄክቶች ይጠናቀቃሉ።