
የላቀ ዕውቀት ያላቸውን ተማሪዎች ለይቶ በማብቃት ለሀገርም ኾነ ለክልሉ ተመራማሪ እና ዓለም አቀፍ መስፈርትን የሚያሟሉ ልሂቃንን ለማፍራት የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ድርሻ ከፍተኛ ነው።
በአማራ ክልል እየተገነቡ ካሉ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል የደብረ ታቦር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት አንደኛው ነው። ይህ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2016 ዓ.ም ነው የተጀመረው። ግንባታው ያለበትን ደረጃ ከአሁን በፊት በአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ መዘገባችን ይታወሳል። አሁን ላይ ግንባታው ተጠናቅቆ ሥራ ለመጀመር ጫፍ ላይ ይገኛል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እየበሩ አዕምሮ የደብረ ታቦር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ መንግሥት በጀት ሲገነባ መቆየቱ አንስተዋል።
ትምህርት ቤቱ አሁን ላይ ግንባታው ተጠናቅቆ ሥራ ለማስጀመር መምህራንን እና የአሥተዳደር ሠራተኞችን ከመቅጠር ባለፈ ለመማር ማስተማር የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን የማሟላት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። የተማሪዎች የመኝታ አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ የቤተ-መጻሕፍት ወንበሮች እና ጠረንጴዛዎችን ጨምሮ በርካታ ቁሳቁሶች ተሟልተዋል ነው ያሉት።
ትምህርት ቤቱ ለማስተማር 200 የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎችን እንደሚቀበልም ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን የመማር ማስተማር ተግባር ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል። አብዛኛዎቹ የግንባታ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን እና ግብዓት የማሟላት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
ይህን ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት መማር ማስተማር ለማስጀመር ከፊል ርክክብ ተፈጽሞ ቁሳቁስ እና የሰው ኃይል የማሟላት ሥራ መሠራቱን ነው የተናገሩት። የመምህራን ቅጥር መፈጽም እና ተማሪዎችን የመመልመል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የቀሩትን የመብራት እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ጉዳዮችን በመፈጸም በቀጣይ ሕዳር/2019 ዓ.ም መማር ማስተማር ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_19_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
