በሐረሪ ክልል የገጠር ወረዳዎች የመንገድ መሠረተ ልማት ዝርጋታ እየተካሄደ ነው።

13

በሐረሪ ክልል በገጠር ወረዳዎች የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከ150 ኪሎ ሜትር በላይ የጥርጊያ እና የጠጠር መንገድ እየተገነባ እንደሚገኝ የሐረሪ ክልል ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢንጅነር ፈርሀን ዚያድ አስታውቀዋል።

የሐረሪ ክልል ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢንጅነር ፈርሀን ዚያድ እንደገለጹት በክልሉ የገጠር ወረዳዎች እየተካሄዱ ከሚገኙ የገጠር መንገዶች ውስጥ በኤረር ወረዳ እየተገነባ የሚገኘውን የኤረር ዶዶታ-ቂሌ የ12 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 20 ሜትር ስፋት ያለው መንገድ አንዱ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ በሚገኙት ሦሥቱም የገጠር ወረዳዎች የጠጠር መንገድ እና ነባር መንገዶችን የማስፋት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

የገጠር መንገድ ግንባታው በክልሉ፣ በፌዴራል እና ከተለያዩ አካላት በተገኘ ድጋፍ እየተገነባ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ በከተማ እና በገጠር የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋት አዲስ ከሚጀመሩ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ነባሮቹን የማደስ እና የማስፋፋት ተግባር በትኩረት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

እየተካሄዱ የሚገኙ የመንገድ ልማት ሥራዎች ለማኅበረሰቡ የሚሰጡት ጥቅም ከፍተኛ መኾኑን ጠቁመዋል። በተለይም አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ እና አስፈላጊ የትራንስፖርት አማራጭ እንዲጠቀሙ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።

ከዚህም ባሻገር አስፈላጊ በኾኑ ጊዜያት የገጠር ነዋሪዎች ፈጣን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መኾኑንም ጠቁመዋል።

የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮች ተደራሽነትን በገጠር አካቢ ለማስፋት የመንገድ ልማቱ ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖረውም አስታውቀዋል።

የገጠር ወረዳዎችን እርስ በርስ የማገናኘት እና ገጠርን ከከተማ የማስተሳሰር ፋይዳ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

የመደመር መንግሥት የመንገድ ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደ ክልል እና በመላ ሀገሪቱ በስፋት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

በመገንባት ላይ የሚገኙ መንገዶች የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በመኾኑ ማኅበረሰቡ በየአካባቢው የተገነቡም ኾነ እየተገነቡ ያሉ የመንገድ ልማቶችን በባለቤትነት መጠበቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኤረር ወረዳ ነዋሪዎች እንደተናገሩት በመደመር መንግሥት እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ኑሯቸውን ለማቅለል እያገዟቸው ነው።

ነዋሪዎች እንዳሉት በተለይ የግብርና ምርቶቻቸውን ለከተማው ተጠቃሚ ለማቅረብ አዲሶቹ የገጠር መንገዶች የተሻለ አማራጭ እና ምቹ አጋጣሚ ፈጥረዋል።

ከዚህ ቀደም ወደ ሕክምና ተቋም በፍጥነት ለመድረስ እና ሕክምና ለማግኘት ይገጥማቸው የነበረውን ችግር በመቅረፍ አስፈላጊውን አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_19_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሩሲያ እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ ይቆማሉ” የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን
Next articleየደብረ ታቦር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በሕዳር 2019ዓ.ም ሥራ ይጀምራል።