
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሩብ ዓመት አፈጻጸሙን ከዞን እና ከተማ አሥተዳደሮች የትምህርት የሥራ ኀላፊዎች ጋር እየገመገመ ነው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ ባለፉት ሦሥት ዓመታት የትምህርት ዘርፉ ትልቅ ስብራት ደርሶበት እንደነበር አንስተዋል። “ዓመቱ ለትምህርት የትንሳኤ እና የአብርኾት መኾን አለበት” ብለዋል።
በክልሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውንም ገልጸዋል። በክረምቱ ወቅት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ራስ በማስቻል፣ የትምህርት ግብዓቶችን በማሟላት እና ከ164 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የማካካሻ ትምህርት በመስጠት ረገድ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
በትምህርት ዘመኑ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መታቀዱን ያስታወሱት ኀላፊው እስካሁን ከዕቅዱ 73 በመቶዎቹ ወደ ትምህርት ቤት መምጣታቸውን ገልጸዋል።
የቀጣይ ዋና ትኩረትም ተማሪዎችን በማብቃት እና የተማሪዎችን የማለፍ ምጣኔ በማሳደግ ላይ መኾን እንዳለበት አሳስበዋል።
የክልሉ መሪዎች ለትምህርት ትልቅ ትኩረት በመስጠታቸው አሁን ላይ የተመቸ ሁኔታ መፈጠሩን እና ወደ ኋላ ማለት እንደማይገባ አሳስበዋል።
የመማር ማስተማር ሥራውን ከማስቀጠል ጎን ለጎን በትምህርት ዓመቱ በስምንት ሪጆፖሊታንት ከተሞች ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ለመፍጠር እንደሚሠራም ተናግረዋል። ለዚህም በጀት መያዙን እና በሚቀጥለው ዓመትም ሥራው ወደ ዞኖች እንደሚሰፋ ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር መላውን ሕዝብ በማስተባበር የየአካባቢውን ትምህርት ቤቶች ገጽታ ለመቀየር ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ተብሏል።
#የመደመር_መንግሥት#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#አሚኮ #Education #ForChange #Amhara
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_15_2019_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
