የዓባይን ምስጢር የፈታው ትውልድ፤ የባሕር በር ባለቤትነቱን ማረጋገጥ አይሳነውም።

10

 

ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር የትናንትና ታሪኬ ኾኖ አይቀርም የሚል አጀንዳዋን ካነሳች ውላ አድራለች።

የተፈጠረው ስህተት ትላትና ቢኾንም ዛሬ እና ነገ ይታረማሉ የሚሉ አንደበቶች እየበዙ መጥተዋል። ይህ ጉዳይ ተግባራዊ ይኾን ዘንድ ህያው ምስክሮች አሉ። የሺህ ዓመታት ፈተና የኾነው የዓባይ ጉዳይም ተፈትቷልና።

ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ አብራክ ክፋይ እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው። ታሪክ ቀይ ባሕር ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ የተከፈለውን ዋጋ ላይፋቅ በደማቁ ከትቦታል። ያኔ እንቢ ለሀገሬ ያሉ እናት ሀገር ወዳድ ዜጎች ውድ ሕይወታቸውን ሳይሰስቱ እንደሰጡላትም ተመዝግቧል።

ቀይ ባሕርን ዓይናችን እያየ ከሚሄድስ ሞቴን እመርጣለሁ እያሉ ራሳቸውን ለሀገር ክብር የሰጡ መኖራቸውም እንዲሁ ተሰንዷል። የአሰብ ወደብ ከኢትዮጵያ የወጣበትን ስሁት ታሪክ የሰነዱት እና የታሪኩ ተጋሪ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ ‘አይ ምጽዋ’ መጽሐፍ ላይ ይህን ብለዋል።

“በዚች የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በር እና ዓለም አቀፍ ወደብ በኾነችው በምጽዋ ከተማ እና በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ቆሜ ሽጉጤን ለመጠጣት ዝግጁ ነኝ። በእውነት እኔ ዛሬ በሞት ብሸነፍም በታሪክ እና በመጭው የኢትዮጵያ ትውልድ ፊት ግን አልሸነፍም” በማለት ለሀገሩ ዋጋ የከፈለውን እና በወቅቱ የባሕር ኀይል አባል የነበረን ጀግና ውሳኔ በመጽሐፉ አስፍረዋል።

ይህ ውሳኔ ጀግኖች ለአሰብ ጉዳይ ጽኑ አቋማቸውን እስከ ሞት ድረስ በተግባር ለመግለጣቸው ምስክር ነው።

ከዚሁ “አይ ምጽዋ” መጽሐፍ ላይ “ኢትዮጵያ ሀገሬ የጀግኖች መፍለቂያ እና ታሪክ ያላት ሀገር ናት፤ ጀግናው ሕዝቧ እያለ የባሕር በሩ በሻዕቢያ ተይዞ እና የጠላቶቹ መፈንጫ ኾኖ አይቀርም” የሚል ጠንካራ ሃሳብም ሰፍሮ ይገኛል።

በወቅቱ የባሕር ኀይል አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል ተሾመ ተሰማ “የፈለገውን ያህል ጊዜ ይቆይ እንጂ ሻዕቢያ ምጽዋን እንደያዛት ለዘለዓለም አይኖርም” ማለታቸውንም ጽፈዋል።

ይህ ኢትዮጵያ የባሕር በሯ ከጇ ሲወጣ በወቅቱ የነበሩ የባሕር ኀይል አባላት እና ተቆርቋሪዎች የሕይወት ዋጋ እየከፈሉም ለቀጣዩ ትውልድ አደራን እያስቀመጡ፤ ታሪክን በደማቸው እየጻፉ ለመሄዳቸው ማሳያ ነው።

👉 ታድያ ለሀገራቸው ሲሉ ቀይ ባሕር ላይ የወደቁት ጀግኖች አደራ ተቀባዩ ትውልድ ማን ይኾን?

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል በአንድ ወቅት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ያጣችው ዛሬም ድረስ ባሉ ጠላቶቿ ነው ብለዋል። በዋናነትም ጥንተ ጠላቷ ግብጽ ለኢትዮጵያ የባሕር በር አልባነት እጇ አለበት ባይ ናቸው።

ትናንት ብቻ ሳይኾን ዛሬም ኢትዮጵያ የባሕር በርን ስታነሳ ግብጽ የሴራዋ ማገርሸት ፍትሐዊ ጥያቄን የማጥፋት ዘዴዋ እንደኾነ አንስተዋል።

ግብጻዊያን ባሉበት የዓለም ሀገራት ሁሉ ለሀገራቸው ዲፕሎማት ናቸው፤ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችንም የመጠቀም ነገራቸው ብልጠት የተሞላበት እንደኾነ ነው የገለጹት። ዓባይ ላይ ተንኮሏ የከሸፈባት ግብጽ ዛሬም እንደትናንቱ በየመድረኩ ክሷን ያለማቆሟ ምስጢር ይኸው ነው ብለዋል።

ከመሐመድ አሊፓሻ ጀምሮ የግብጽ መሪዎች ሁሉ ኢትዮጵያን ለማዳከም ያልሠሩት ተንኮል የለም ነው ያሉት። ከ4 ሺህ በላይ ሚዲያዎች በግብጽ ውስጥ ይገኛሉ የሚሉት ፕሮፌሰሩ እነዚህ ሚዲያዎች ሁሌም ኢትዮጵያን በሀሰት መወንጀል አንዱ ሥራቸው ኾኖ ቀጥሏል ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሀገሩ ዲፕሎማት መኾን አለበት የሚሉት ፕሮፌሰሩ ለአብነት እንኳ የቀይ ባሕር የትናንት ማንነት ላይ ስንቶቻችን ጠንቅቀን እናውቅ ይኾን? ይላሉ።

ያም ኾነ ይህ ብዙ ታሪክ ቀያሪ የኾነውን ሕዳሴ ግድብን እውን ያደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀይ ባሕርን በክብሩ ለመመለስ ያዳግተዋል ብዬ አላምንም ነው ያሉት ፕሮፌሰር አደም ካሚል። ትውልዱም ታሪክ ለመጻፍ የታደለ መኾኑን አምኖ መዘጋጀት እና መተባበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_15_2019_ዓ_ም

👉በሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🔥ባለምጡቅ አዕምሮዎቹ ሕዳሴ ዘመኑ እና ሙባረክ ሙሐመድ በክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ተሸልመዋል!
Next articleየአዳኝ ክንፍ ባለቤቱ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት!