“እኛ የኮሪደር ልማት ሥራውን እስከ ምሽት ድረስ ሥንሠራ እናንተም ሱቆቻችሁን እና ሆቴሎቻችሁን በጊዜ ዘግታችሁ አትሂዱ” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

4
ባሕር ዳር ኮሪደሯ ውበትን፣ መብራቶቿ ድምቀትን፣ የዓባይ እና ጣና ኅብረት ልዩ ምልክትን፣ አየሯ ልዩ ምቾትን ሰጥተዋታል። ዘንባባዎቿ ደግሞ የመገለጫዋ መልኳ ናቸው። የጣና ገዳማት ልዩ የታሪክ ማኅደርነትን፣ የቤዛዊት ኮረብታ እና የድባንቄ ተራራ ልዩ ትዕይንትን ፈጥረውላታል።
ከአመሠራረቷ ጀምሮ ጥበበኛ እጆች የከተማ ፕላን አውጥተው የቆረቆሯት፣ አሁንም የከተሞችን ሕዳሴ ያበሰረው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ይበልጥ ውብ አድርገዋታል።
ባለፈው ዓመት በከተማዋ ከ19 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት ተሠርቶላታል። በሰፋፊ የአስፋልት መንገዶቿ ላይ የእግረኛ፣ የብስክሌት፣ የአረንጓዴ ውበት እና ዘመናዊ መብራቶች ተጨምረውላት አዲስ እና ማራኪ ገጽታን ተላብሳለች። ቆየት ብሎ ለሚያውቃት አሁን አዲስ ከተማ ኾናለች። በጎበኟት ሁሉ አዕምሮ ውስጥ ልዩ ትውስታን ታስቀምጣለች።
የከተማዋ ልማት ዛሬም ቀጥሏል። በ2019 በጀት ዓመት የሚሠሩ የልማት ሥራዎች ተበስረዋል። ከእነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች መካከልም ከድባንቄ መድኃኒዓለም እስከ አዲሱ ዓባይ ድልድይ የሚዘልቅ 7ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኮሪደር ልማት ተጀምሯል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እንደተናገሩት ከተማዋን ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ከተጀመረው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በተጨማሪ የጣና እና የዓባይ ዳርን ለማልማት የጥናት እና የዲዛይን ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ባሕር ዳር የሰላም እና የልማት ከተማ መኾን አለባት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው “24 ሰዓት የልማት እንቅስቃሴ የሚደረግባት ከተማ መኾን አለባት” ብለዋል። የቱሪዝም ከተማ በመኾኗ ያልተገደበ የ24 ሰዓት እንቅስቃሴ የሚደረግባት፣ 24 ሰዓት ኢኮኖሚ የሚመነጭባት ከተማ መኾን እንዳለባትም ተናግረዋል።
“እኛ የኮሪደር ልማት ሥራውን እስከ ምሽት ድረስ ስንሠራ እናንተ ሱቆቻችሁን እና ሆቴሎቻችሁን በጊዜ ዘግታችሁ አትሂዱ” በማለት ለነዋሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል። ነጋዴዎች እና ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ነዋሪዎችም እስከ ምሽት ድረስ መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
በተገደበ ሰዓት ተሠርቶ ሕይወት አይቀየርም፣ ኢኮኖሚም አይመነጭም ብለዋል። ይህንን ማሻሻል እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል።
በቀጣይ ማሻሻያዎችን በማድረግ በጊዜ በሚዘጉ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ ወደ እርምጃ እንደሚገባም አመላክተዋል።
✍️በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የሕዝብ ልጅ የኾነው መከላከያ ሠራዊት ለሚያከናውነው ሀገር የማዳን ተግባር በጽናት ከጎኑ እንቆማለን” የደሴ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች
Next articleለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን የኾነው የደሴ ሕዝብ ድጋፉን ለሠራዊቱ ለማሳየት አደባባይ በነቂስ ወጥቷል።