በቴክኖሎጅ የዘመነ፣ ለሰንደቁ የታመነ!

7
የሀገርን ሉዓላዊነት እና ዘላቂ ደኅንነት የማረጋገጥ ታሪካዊ ኀላፊነት የዘወትር ተግባሩ ነው። በጽኑ እና ባልተናወጠ ወታደራዊ አቋም የተገነባ የክብር መሠረትም ነው።
እርሱ በአፍሪካ ቀጣና ውሥብሥብ የጂኦፖለቲካዊ ውጥረት እና የኀይል አሰላለፍ ሚዛኑ ባየለበት በዚህ ፈታኝ ወቅት የሰው ኀይል ብዛት ብቻውን በቂ አይደለምና የላቁ እና የመጠቁ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ታጥቋል፤ በከፍተኛ ወታደራዊ ሥነ-ምግባር የታነጸ ነው፤ በአውደ-ውጊያ ጥበብም የተካነ የሀገር ምሰሶ ነው።
የውጊያ ዝግጁነቱ ወደር የለውም። የሀገሩን ታሪካዊ ጠላቶች እስስታዊ ሴራዎች እና የቀጣናውን ስስ ገጽታ ጠንቅቆ የተረዳ ነው። የትኛውንም ውሥብሥብ የፈተና ማዕበል መጋፈጥ የሚያስችል ወታደራዊ አቅምንም ገንብቷል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገረ-መንግሥት ሕልውና ዘብ ብቻ አይደለም ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ሁሌም በንቃት የቆመ የማይበገር ጋሻ ነው።
ይህ ሁሉ ብቃት እና ዝግጁነት የጦር ሜዳ ውሎው ድል አድራጊ እና አሸናፊነት እውነተኛ ምሥጢርም በማይናወጥ ሕዝባዊ ድጋፍ እና ሥነ-ልቦናዊ ትስስር እንዲሁም በረቂቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ውስጥ የታሰረ መኾኑ ነው።
ይህ ጥልቅ ሕዝባዊ ጥምረት ሠራዊቱ አስቸጋሪ እና ፈታኝ ሁኔታዎችን በጽናት እና በቁርጠኝነት እንዲሻገር የሚያስችለው ታላቁ የመንፈስ ትጥቁ ነው።
የሠራዊቱን ሁለንተናዊ አቅም በተመለከተ የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሲያስረዱ “የሠራዊቱ ግንባታ ሂደት በመሣሪያ እና በቴክኖሎጂ መዘመን ላይ ብቻ የተገደበ ሳይኾን በሰው ኀይል አዕምሯዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ብቃት፣ በወታደራዊ ዲሲፕሊን፣ በተግባራዊ ዝግጅት እና በውጊያ አፈጻጸም ጥራት ላይ ያተኮረ ነው” በማለት ይገልጹታል።
ከዚህም በተጨማሪ የትዕዛዝ ሰንሰለቱን በጽናት የጠበቀ፣ በሙያዊ ዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን ማመንጨት እና የሕግ ሥርዓትን ማክበር የተቋሙ ዋነኛ ስልታዊ አቅጣጫዎች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ሠራዊቱ ማንኛውም ሀገራዊ አደጋ በተደቀነበት ቅጽበት ተገቢውን እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የሰው ኀይል፣ የመረጃ መዋቅር እና የአመራር ቅንጅት በአንድ ላይ አስተባብሯል።
የተጣለበትን ሀገራዊ አደራ በተግባራዊ ቅንጅት በመወጣትም ተልዕኮዎቹን በስኬት የመቋጨት ብቃትን ተክኗል። የጦር ሜዳ ውሎው የሚያሳየው የውጊያ ጥበብ እና ብቃት ለሀገራዊ ደኅንነት ብቻ ሳይኾን የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት ጭምር የሚወስን ትልቅ ኀይል ነው።
በአጠቃላይ ሠራዊቱ በትንሽ መስዋዕትነት እና ኪሳራ ታላላቅ የውጊያ ድሎችን የሚጎናጸፍ፣ በዓለም አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች እና በቀጣናዊ የደኅንነት ሥራዎች የታመነ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ኾኖ ዘልቋል።
ሠራዊቱ በቴክኖሎጂ የዘመነ፣ በዓላማ ጽናት የታነጸ፣ በተግባራዊ ስልት የላቀ እና የሕዝብ ተአማኒነትን ያተረፈ የሰላም ምሰሶ ነው፤ ዛሬም ነገም ለሀገር ሕልውና ዘብ በመቆም ተቋማዊ ግንባታውን እና ሕዝባዊ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል።
✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleኢትዮጵያ – የነጻነት ቀንዲል ሀገር፣ ለቀጣናውም የመረጋጋት ዋስትና!
Next article“የጣና ፎረም እና ባሕር ዳር ለዓመታት የዘለቀ ትስስር አላቸው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)