የማያረጀው የኢትዮጵያውያን ጀግንነት በዓባይ ሉዓላዊነት ላይም ታድሷል!

7
ግብጽ የዓባይን ምንጭ በብቸኝነት ለመቆጣጠር የተንኮል መረቧን አስፍታ ተደጋጋሚ የጥፋት ዘመቻን በኢትዮጵያ ላይ አካሂዳለች። የተንኮል ጥፋቷ ግን በኢትዮጵያውያን የማይበገር የጀግንነት አለት ላይ እየተላተመ ከሽፏል። ይህም ከትናንት የደም ታሪክ እስከ ዛሬ የልማት አርበኝነት በተጨባጭ የተንጸባረቀ ሀቅ ነው።
በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ በጉንደት እና በጉራዕ ጦርነቶች የግብጽን ዘመናዊ ወራሪ ኅይል ድባቅ በመምታት ያሳፈረበት ታሪክ ዛሬም በድምቀት ይንጸባረቃል።
የግብጽ ቀጥተኛ የወረራ ሙከራ በኢትዮጵያውያን የነጻነት ተጋድሎ እና ወደር የለሽ የጦር ስልት እንዴት እንደተቀለበሰ እና ግብጽን ከቀጥታ ጦርነት ወደ ኋላ እንድትል እንዳደረጋት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እና ሌሎችም የታሪክ ምሁራን በመጽሐፎቻቸው ምስክርነትን አስቀምጠዋል።
በቀጥታ ወረራ አቅሟ የተንኮታኮተው እና የኢትዮጵያውያንን ክንድ ያየችው ግብጽ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስትራቴጂዋን በመቀየር ወደ እጅ አዙር ጦርነት፣ የዲፕሎማሲ ሴራ እና የሐሰተኛ መረጃ ዘመቻዎች ተሸጋግራለች።
በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ምርምር በማድረግ የሚታወቁት ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤርሊክ የዓባይ ወይም የናይል ወንዝ አወዛጋቢነትን በተመለከተ ጽፈዋል። (The Cross and the River:- Ethiopia, Egypt, and the Nile) በተሰኘ መጽሐፋቸው እንዳብራሩት ግብጽ ከ85 በመቶ በላይ የዓባይ ውኃ ምንጭ ከኾነችው ኢትዮጵያ ላይ ያላት ሙሉ ጥገኝነት ከፍተኛ የህልውና እና የሥነ-ልቦና ስጋት ፈጥሮባታል።
ስጋቷንም ለመቅረፍ እና የውኃውን መነሻ ለመቆጣጠር በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀጥተኛ ወረራ አድርጋ በጉንደት እና በጉራዕ ተሸንፋለች።
ብርጋዴር ጀኔራል ካሳዬ ጨመዳ በአንድ ወቅት የመሰከሩትም ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ 15 ጊዜ ቀጥተኛ ወረራ አድርጋ ሁሉንም በሽንፈት አጠናቅቃለች።
ቀጥሎም ስትራቴጂዋን ወደ እጅ አዙር ጦርነት በመቀየር በኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በርስ ግጭት እና አለመረጋጋት እንዲፈጠር እየሠራች ትገኛለች።
ከእጅ አዙር የጥፋት ሴራ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ያገለሉ የ1929 እና የ1959 የቅኝ ግዛት ውሎችን በማጽደቅ፣ የአስዋንን ግድብ በመገንባት የውኃ የበላይነቷን ለማስጠበቅ ያደረገችውን ተከታታይ የታሪክ ሴራ ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤርሊክ በመጽሐፋቸው አሳይተዋል።
ከቀጥተኛ እስከ እጅ አዙር ጦርነት እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክ በኢትዮጵያ የተሸነፈችው ግብጽ ዛሬም በኤርትራ በኩል ታጣቂዎችን በመደገፍ እና የሐሰተኛ ትርክቶችን በማራገብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመፈታተን ሙከራ እያደረገች ነው።
የግብጽ የዘመናት የእጅ አዙር ጦርነትም ኾነ የፕሮፓጋንዳ ጩኸት ከትላንት አባቶቹ የጀግንነት ወኔን የወረሰውን የአሁኑን ትውልድ ሊያቆመው አልቻለም። ኢትዮጵያ የውኃ ሃብቷን በፍትሐዊነት የመጠቀም መብቷን አስጠብቃ፣ የማንንም ተጽዕኖ ተቋቁማ፣ ዛሬም በድል እና በአሸናፊነት ጎዳና ላይ ጸንታ ትገኛለች።
✍️ ስማቸው አጥናፍ
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሻብያ ሴራ እና የኢትዮጵያ የማይናወጥ ጽናት
Next articleኢትዮጵያ – የነጻነት ቀንዲል ሀገር፣ ለቀጣናውም የመረጋጋት ዋስትና!