ዘላቂ ሰላም እና ልማት የሚረጋገጠው በመሪዎች ቁርጠኝነት እና በጠንካራ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ነው።

7
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ከእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በከተማዋ ልማት እና ዘላቂ ሰላም ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በአካባቢ ጥበቃ እና በተለያዩ አደረጃጀቶች በመሳተፍ ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የኑሮ ወድነትን ማረጋጋት፣ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ የመብራት እና የንፁህ መጠጥ ወኃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ከመንግሥት የሚጠበቁ ተግባራት መኾናቸውንም አንስተዋል።
የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ኑርልኝ ሰውነት ከማኅበረሰቡ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ በሚኾን ወጪ ሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለመተግበር እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት ቀሪ ሥራዎች ማጠናቀቅ እና ተጨማሪ አንድ ኪሎ ሜትር ለመገንባት መታቀዱንም አንስተዋል።
በውይይቱ የተነሱ ሁሉንም ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በመመለስ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሠራልም ነው ያሉት።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋሁን ተሰማ የእንጅባራ ከተማ እና አካባቢው ማኅበረሰብ ከጸጥታ ኀይሉ ጎን በመሰለፍ በከፈለው የሰላም ዋጋ በአካባቢው የሰላም ሁኔታ እየተሻሸለ መምጣቱን ተናግረዋል።
ሰላምን ከማጽናት ጎንለጎን መንግሥት በ7ኛው ምርጫ ለሕዝቡ የገባውን ቃል በተግባር ለመግለጥ በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አየን ብርሃን ሰላም እና ልማት የአንድ ሀገር የብልጽግና መሠረቶች መኾናቸውን ገልጸዋል። ይህ የሚረጋገጠው ደግሞ በመሪዎች ቁርጠኝነት እና በጠንካራ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ነው ብለዋል።
ኅብረተሰቡም ለከተማዋ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በመድረክ አረጋግጧልም ነው ያሉት። ከእጅ መንሻ የፀዳ ግልጽ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት አገልግሎት እንዲኖርም በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የከተማዋን ዕድገት እና የሕዝቡን ፍላጎት የሚመጥኑ የመሠረተ ልማቶችን ተደራሽ ማድረግ በቀጣይ በትኩረት የሚፈጸሙ ተግባራት መኾናቸውንም አንስተዋል። ሀገር የሚገነባው በአሉባልታ ሳይኾን በጠንካራ የሥራ ባሕል ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የሕዝቡ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መኾን እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
ኅብረተሰቡ የቀደመ አብሮነቱን በማጽናት ለጋራ ብልጽግና መትጋት እንደሚገባውም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሀገራችን ኩሩ ኾና የቆመችው በመከላከያ ሠራዊት ክንድ ነው።
Next articleየሻብያ ሴራ እና የኢትዮጵያ የማይናወጥ ጽናት