ወርቅ የሚገባቸው እናቶች ስለምን የአፈሙዝ ጩኸት ይስሙ?

21

 

የበጋውን ሙቀት ተቋቁማ፣ በክረምት ጭቃው እና ቁሩ ሳይበግራት ለስጋዎቿ ክፋይ የወደፊት ሕይወት ስትል የምትማስነው እናት ለልጆቿ ስትል የምትከፍለው ዋጋ ከሁሉም የተለየ ነው።

የማዕድ ቤቱ ጭስ ዓይኗን እያቃጠላት፤ ልጇን በጀርባዋ አዝላ ምግብን ታበስላለች። የልጇን ሕመም ታማ፤ ሳቁን ስቃ፤ ለቅሶውን አልቅሳ መከራ እና ስቃዩን ችላ ልጇን ታሳድጋለች።

“ከልጆቼ በፊት እኔን” እያለች ደስታቸውን እንጅ ሀዘናቸውን እንዳታይ ዘወትር ፈጣሪዋን ትለምናለች። እናቶች ልጆቻቸው በመልካም ስብዕና አድገው እንዲጦሯቸው፣ በመልካም ሥራቸው ስማቸውን እንዲያስጠሩላቸው፣ ለማኅበረሰቡ ኩራት፣ ለሀገሩ ደግሞ ስኬታማ ተግባርን እንዲከውኑ ይመኛሉ።

ዳሩ ግን እናቶች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ያሳለፉት የፈተና ዘመን እና ድካም ከንቱ ሲኾን ደግሞ አንገታቸውን ይደፋሉ።

በተለይም በሀገር ጥፋት ላይ ልጆች ተሳታፊ ሲኾኑ ሀዘናቸው እጥፍ ድርብ ይኾናል። በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ደግሞ የእናቶችን ሀዘን አክብዶት ቆይቷል።

የሕዝብን ጥያቄ እናስመልሳለን ያሉ ታጣቂዎች በርካታ እናቶች ልጆቻቸውን እንዲያጡ፣ በአፈሙዝ ጩኸት እንዲረበሹ፣ የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኙ፣ በሩቅ ያሉ ልጆቻቸውን እንዳያዩ፣ በነጻነት ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓቸው ቆይቷል።

ለራሳቸው ተጎሳቁለው ልጆቻቸውን ያደመቁ እናቶች መጥፎ መንገድን በመረጡ ታጣቂዎች በእንባ ታጥበዋል።

ለልፋታቸው ወርቅ፣ ለመድመቂያቸው ነጭ ቀሚስ ሲገባቸው የአፈሙዝ ድምጽን ይሰሙ ዘንድ ተፈርዶባቸው ቆይቷል። በክልሉ ግጭት እንዲቆም፣ ሰላም እንዲሰፍን እናቶች ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ስለ እናቶች ድካም ሰላምን ማጽናት፣ የሰላምን አማራጭ መቀበል፣ የአፈሙዝ ላንቃን መዝጋት ከታጣቂዎች እና ከሁሉም ማኅበረሰብ የሚጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር ነው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣውን የክልሉን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማስቀጠል እና የእናቶችን የሰላም ተማጽኖ መቀበል ከታጣቂዎች ይጠበቃል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደብረ ማርቆስ የአየር ማረፊያ ምርቃት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በአማራ ሕዝብ እየማሉ ሕዝብን የሚያደናግሩ፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች ህልም ተጋርተው የሕዝብን ስቃይ የሚያራዝሙ አሜካላዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

የታጠቁ አካላትን ለማስቆም ከመንግሥት ባሻገር ሕዝቡ የበኩሉን ኀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል። ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም በቁርጠኝነት ማጽናት እንዳለበትም ነው የተናግሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በዚሁ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ንግግር በዓባይ ሸለቆ እና በአሊዶሮ አካባቢ የሸፈተውን ሽፍታ በጋራ ታግሎ ማስወገድ ሲገባን ተጨማሪ ሽፍቶችን ማበራከት ተገቢ አይደለም ማለታቸው ይታወሳል።

የትም ቦታ ያለ ሽፍታ በሕግ እንዲታረም በጋራ በመሥራት የሕዝብን ሰላም እና ልማት ማረጋገጥ ይገባል ነበር ያሉት። የሚለያየንን ነገር እየተወያዩ፣ ጥቃቅኑን ነገር እየረሱ፣ በትልቁ ጉዳይ መሠብሠብ፣ መተባበር እና የሁላችንም የጋራ መሻት የኾነውን ሰላም እና ልማት በጋራ ለማሥፈጸም መጣር ይበጃል ብለዋል።

ይህ ሲኾን በቀየው ሰላም ይሰፍናል፤ ሀገር ደህና ትኾናለች፤ ሕዝብም በዘላቂነት እፎይ ይላል፤ የእናቶች እንባም ታብሶ የተጨነቀ ገጻቸው በደስታ ይሞላል። ስለዚህ አሁንም ቢኾን በጫካ የሚንቀሳቀሱ ቀሪ ታጣቂዎች በሙሉ ስለእናት ሀዘን እና ስለሕዝብ ልመና ብለው የሰላም አማራጩን ፈጥነው መቀበል ይጠበቅባቸዋል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_07_2019_ዓ_ም

✍️ በያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ከሕሊና ባለዕዳነት ወደ ሥራ ተመልሰናል” የቀድሞ ታጣቂዎች
Next articleመከላከያ ሠራዊት የጀግንነት እና የሀገር ክብር መሠረት!